Written by ናፍቆት ዮሴፍ (ከፍኖተ ሰላም)
“ከእነ ቤተሠቤ እዚህ ለመድረስ ያየሁትን ፈተና ፈጣሪ
ያውቀዋል፡፡ ቤተሰቤ ከቁጥር ሳይጐድል ለአገሬ መሬት በቅቻለሁና ከእንግዲህ የፈለገው ይሁን” አሉኝ፤ ከቤኒሻንጉል
ክልል ያሶ ወረዳ ተፈናቅለው በፍኖተ ሰላም ድንጋያማ መጠለያ ውስጥ ያገኘኋቸው አዛውንት፡፡ በአማራ ክልል የከሠላ
ወረዳ ተወላጅ የኾኑት አዛውንት፤ ኑሮ አልቃና ቢላቸው በ1997 ዓ.ም ሦስት ልጆቻቸውን ከትዳር አጋራቸው ጋር
ይዘው፣የትውልድ ቀያቸውን ለቀው የተሻለ ሥራ ይገኝበታል ወደ ተባሉበት ቤንሻንጉል ክልል ያቀናሉ፡፡ ኑሮአቸውንም
በቤኒሻንጉል ክልል ካደረጉ በኋላ ተጨማሪ አራት ልጆችን አፍርተው የቤተሠባቸውን ቁጥር ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደርጋሉ፡፡
ላለፉት ስምንት ዓመታት ቀን ከሌት እየሠሩም ኑሮአቸውን መምራት ይቀጥላሉ፡፡ ለዓመታት ከኖሩበት መንደር በድንገት
እንዲለቁ ሲገደዱ ግራ የተጋቡት አዛውንት የስምንት ልጆች አባት በመኾናቸው ሲፈናቀሉ ከፍተኛ ውጣ ውስጥ ከተታቸው፡፡
በቀላሉ የሚሳካላቸው አልኾነም፡፡ ‹‹ ከያሶ ወረዳ ውጡ ተብለን
ድብደባና እንግልት ሲደርስብን እንደ ሌሎቹ እመር ብዬ መሸሽ አልኾን አለኝ፡፡ ልጆቼንና ባለቤቴን እንዴት
ላድርጋቸው? ከአንድ ቤት ዘጠኝ ሰው የትስ ነው መውደቂያችን? ስል ጭንቀት ገባኝ›› የአዛውንቱ ዐይኖች እንባ
አቀረሩ፡፡ አሁን አዛውንቱ ብዙ ስቃይ አልፈው በአማራ ክልል ፍኖተ ሰላም ከተማ ከሌሎች 3500 ተፈናቃዮች ጋር
ከእነ ቤተሠባቸው በችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በሚኖሩበት አካባቢ የእርሻ ቦታ ባለማግኘታቸው የተሻለ ሥራ ፍለጋ
ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ኑሮአቸውን ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያዛወሩ የአማራ ተወላጆች ካለፉት ሦስት
ሣምንታት ጀምሮ በወረዳው ባለሥልጣናትና ፖሊሶች ከቀያቸው ተፈናቅለው በምስራቅ ጎጃም በጀቢጠናን ወረዳ ፍኖተ ሰላም
ከተማ በሚገኝ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ በደረሰን ጥቆማ መሰረት ወደዚያው አመራን፡፡
ከመጠለያው ወዲህ ከንፈሯ ክው ብሎ ደርቋል በጥቁር መናኛ ሻሽ
እራሷን ጠፍንጋ አስራዋለች፡፡ የለበሠችው ቀሚስ ዳር ዳሩ ተተልትሏል፣ የተጫማችው ላስቲክ ጫማ ብዙ ቦታ
ተበሣስቷል፡፡ በጠይም መልኳ ላይ ድካምና ተስፋ መቁረጥ ይነበብባታል- በፍኖተ ሰላም ከዳሞት ሆቴል ጀርባ ከአውቶብስ
መናህሪያ ዝቅ ብሎ ባለው ‹‹ፍቶተ ሠላም›› ክሊኒክ መግቢያ በር ላይ ያገኘኋት የ27 ዓመቷ ወጣት የአራት ወር
ነፍሰ ጡር ናት፡፡ በጉዞዋ በደረሰባት እንግልት በመታመሟ ከመጠለያው ለህክምና ወደ ክሊኒኩ እንደመጣች ነገረችኝ፡፡
“ራሴን ያዞረኛል፣ ሰውነቴን በጠቅላላ ይቆረጥመኛል፣ ያስለኛል፣ በተለይ ሌሊት ሌሊት እንቅልፍ የለኝም” የምትለው
ነፍሠ ጡሯ፤ ባደረገችው ምርመራ ደም ማነስ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳጋጠማት ተነግሯታል፡፡
ባለቤቷም የታዘዘላትን መድሀኒት ሊገዛ ሄዷል፡፡ “ቀን ፀሀዩ፤
ማታ ብርዱ በዚያ ላይ ያለ ምንጣፍ ጠጠር ላይ እየተኛሁ ነው ለበሽታ የተጋለጥኩት፡፡ ከዚህ ቦታስ በሕይወት የምገኝ
አይመስለኝም” አለች፡፡ ባለቤቷ ተመልሶ ሲመጣ ጨዋታው አላማረውም፡፡ ማንነቴን ጠይቆኝ ከተረዳ በኋላ፤ “እዚህ ያሉ
የከተማው አስተዳደሮችና የክልሉ ኃላፊዎች አሁን ያለው ችግር እስኪፈታ ለማንም አትናገሩ ብለውናል” አለኝ፡፡
‹‹አንዳንድ ጋዜጦች ከመካከላችሁ ያልሆነ መረጃ እየወሠዱና እየጻፉ ጋዜጣ ማሻሻጫ አድርገዋችኋል፤ ስለዚህ ዝም በሉ
ተብለናል” የሚል ምላሽ ሠጠኝ፡፡ ችግሩን እንዲነግረኝ ለማግባባት ሞከርኩ፤ “ዋ! ለሠው ቢያወሩት መፍትሄ ካልመጣ
ምን መላ አለው እህቴ?” በማለት መልሶ ጠየቀኝ፡፡ በእግራችን እየተጓዝን መጠለያው አካባቢ ደርሰን ነበርና ባለቤቱን
ወደመጠለያው አስገብቶ አቧራማው ሜዳ ላይ ተቀምጠን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ገባን፡፡ በሙሉ ለማንበብ እባከዎን እዚህ ላይ ይክፈቱት!
No comments:
Post a Comment