I am ambitious to see a true democracy, justice and equality particularly in Ethiopia and generally in the world.
Pages
Yakob's Point of Views and News, Ethiopian politics and News, Cultures, Musics etc
Saturday, November 17, 2012
ኢትዮጲያዊ ኡሴን ቦልት የራሱን ሪኮርድ ኣሻሻለ !
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
ለለውጥ ያህል ለምን አንባቢን ፈገግ ልታደርግ በምትችል የአዲስ አበባ ዘመነኛ ቀልድ አልጀምርም?
አንድ የወያኔ ከፍተኛ ባለሥልጣን በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ሲዝናና ያመሻል፡፡ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት
አካባቢ ሲሆን ወደቤቱ ሊሄድ ቄንጠኛ ፕራዶ መኪናውን ሊያስነሳ ቢሞክር ያልታሰበ ብልሽት
ያጋጥመውና ሞተሩ ለመነሣት እምቢዬው ይለዋል፡፡ ቢለው፣ ቢለው አልሆነለትም፡፡ ከዚያም ሌላ ምርጫ
ሲያጣ ላዳ ታክሲ ያስጠራና ወደቤቱ እንዲያደርሰው ሹፌሩን ይጠይቀዋል፡፡ በቅድሚያ ግን በስንት
እንደሚያደርሰው ሒሳቡን ለማወቅ ይፈልግና “ለቡልጋሪያ ማዞሪያ ነው ቤቴን፣ በስንት ነው
እንዴ’ምታደርሰኝ?” ይለዋል፡፡ ይህ ባለታክሲም ብዙም ሳያቅማማ “150 ብር ይከፍላሉ፤ ይግቡ” ይልና
ጋቢናውን ይከፍትለታል፡፡ ይሄኔ ባለሥልጣኑ ተገርሞ “ቧይ! ለቡልጋሪያ ማዞሪያ ለዚህን ያህል ቡዙ ገንዘብ
ማለተይ ለሞቶ ሃምሳ ብር ከጠየቅኸኝ መ‚ለ ብልህ ስንት ልትለኝ ነው እንዴ?” ይለዋል፡፡ ያ አራዳ
የአዲስ አበባ ላዳ ታክሲ ሹፌር ቀበል ያደርግና “ ጌታዬ፣ የማይመለሱ ከሆነ በ50 ብርም ቢሆን
እወስደወታለሁ!” አይለው መሰላችሁ? ባለጌ ሹፌር፡፡ አሸባሪ ብሎ ዘብጥያ ማውረድ እሱን ነበር፡፡ “በዚህ
ዚቅ ፈገግ ካላሉ ወያኔ ነዎ” የሚል ቅብጠት የሌለብኝ መሆኔን በታላቅ ትህትና ከመግለፅ በተጓዳኝ የሐሳብ
ፈረሴን ልኮልኩልና ንቅድሚት ልሸምጥጥ - ማሣቅና መሣቅ ዱሮ ቀረ፡፡ ዛሬ ሁሉ ነገር አርቲፊሻል ሆኖ
እውነተኛ ፈገግታ ጠፍቷል ወዳጄ፡፡ እንዲያው ነው የምናገጥ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያው መቶ ብር መጠሪያ ዑሴይን ቦልት(Usain Bolt) መባሉን
ሳትሰሙ አትቀሩም ብዬ ልገምት፡፡ ዑሴይን ቦልት ደግሞ በ(እዚች ቦታ ስደርስ ባለቤቴ ‹አሁንም
ደገሙልህ› አለችኝ፤ ምን? እነማን? እመለስበታለሁ፡፡ አላበዙትም?) ዑሴይን ቦልት ደግሞ በዓለም የመቶ
ሜትር ሩጫ ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይይዝ የሰው ቺታ(አቦሸማኔ?) ነው፡፡ የሀገራችን መቶ ብር ከኪስ
ከመውጣቱ እንደወፍ እየበረረ አንዳችም ፋይዳ ያለው ነገር ሳያከናውን በቅጽበት ስለሚያልቅ ስም
ማውጣት የማይገደው የሀገሬ ሰው በተለይ ወጣቱ መቶ ብሩን በዚያ ጃማይካዊ የመቶ ሜትር ሯጭ ስም
ሰየመው፡፡ ግሩም ተመሳስሎ ነው፡፡ አሁን አሁን ደግሞ መቶ ብራችን እንደቦልት በ9 እና 10 ሴኮንዶች
ብቻ ሳይሆን በሁለትና ሦስት ሴከንዶች ድራሹ ሊጠፋ ይዟል፡፡ እንትና እሚባል ተራ ባር ውስጥ አንድ
ሻይ 8 ብር መግባቱን ታውቃለህ? ተራ ሽሮ 50 ብር የገባባቸው ባለምንም ኮከብ ሆቴሎች እንዳሉ
ታውቃለህ? ብርህ ከኪስህ ሾልኮ የጠፋብህ የሚመስልህ ጊዜ መሙላቱንስ ልብ ብለህ ታውቃለህ? ሪከርዱን
አሻሻለ ማለት እንግዲህ ይህን የገንዘብ ዕብደት ለመግለጽ ነው፡፡
ሀገራችን ውስጥ ጉድ እየንተከተከላችሁ ነው ጎበዝ፡፡ ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው መቶ ብር
ማለት ከጥንቱ አንድ ብር ፊት ሊቆም የማይቻለው የማሽላ እንጀራ ሆኗል፡፡ በዘመነ ኃይለ ሥላሤ አንድ
ኩንታል ነጭ ጤፍ ከነማስፈጫው 12 ብር ከሃያ አምስት ሣንቲም እንደነበረ ትናንት አንድ ሰውዬ
አጫውቶኛል፡፡ ይህ ሰው 62 እና 63 ዓመተ ምሕረቶችን በማጣቀስ እንደነገረኝ ከሆነ የምግብ ዘይት፣
ስኳር፣ ላምባ፣ ሥጋ፣ ቅቤ፣ የሰላሱት እህሎች፣ ጥራጥሬዎች፣ ልብስ፣... በኪሎም ይሁን በሊትር ወይም
በሥፍርና በሜትር በዝቅተኛ የመነሻ አሃዳቸው ከአንድ ብር እጅግ በሚያንስ ቁርጥራጭ ሣንቲሞች ይገዙ
እንደነበረና ነገር ግን ሣንቲሞቹን ለማግኘት ለብዙዎች ዜጎች ይከብድ እንደነበረ ቁጭት በሚነበብበት
ትዝታ ተውጦ አውግቶኛል፡፡ ዛሬ እንኳን አንድ ብር መቶ ብር ራሱ ግርማ ሞገሱን አጥቶ የተሙን(አንድ
ሣንቲም) ያህል ወድቋል፡፡ ዱሮ በአንድ ወይ በሁለት ተሙኖች የሚገዛ ዕቃ ነበር - በተለይ አሥመራ
ላይ፡፡ ተሙን አይናቅም ነበር፡፡ በልጅነታችን ተሙኖችን እያጠራቀምን አራትና አምስት ሲደርሱ
እንጠቀምባቸው እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡(በነገራችን ላይ ከደርግ ጀምሮ ሥራ ላይ በዋለው የአሁኑ አንድ
ብር ላይ ምስሉ የሚታየው ባለፈገግታው እረኛ ከዚህ ዓለም እንደተገላገለ ዛሬ ሰማሁ፡፡ ነፍሱን ይማር፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከመኖር ይልቅ መሞት እሚያስቀናበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡)
ዛሬ ኑሮው ሰማይ ደርሷል፡፡ ድሃ መኖር አልቻለም፡፡ የተፈጠረው ሁለት መደብ ብቻ ነው - ሦስት
መደብ የነበረው ቀረ፡፡ ያለውና የሌለው ተብሎ በሁለት ሊከፈል የሚችል መደብ ነው ዛሬ የተፈጠረው፡፡
ሕንድ ወደኢትዮጵያ ገባች፡፡ ይህ ዓይነት የኑሮ ውድነት እንዳለ እንሰማ የነበረው በሕንድ ሀገር ነበር፡፡
የጥንቱ ንዑስ ከበርቴ እየተባለ ሲንቆላጰስ የነበረው መደብ(class) ዛሬ ጠፍቷል፡፡ አንድም ኅሊናውን
እየሸጠ ወደላይኛው የአጭበርባሪዎች ጎራ ተቀላቅሏል አለዚያም ወደለየላቸው ያጡ የነጡ ድሆች ወርዶ
ተመሳስሏል፡፡ በደህናው ዘመን ከኮሌጅ እንደወጣ በወር የቀስ በቀስ ክፍያ (installment) አዲስ ኦፔልና
ከሴፈሪያን ኩባንያ ውኃ ያልነካት ቮልስዋገን እየገዛ በራሱ መኖሪያ ቤት እየኖረ ሠርክ በግሩም የሎንዶን
ሱፍ ይሽሞነሞን የነበረው የዚያኔው ንዑስ ከበርቴ ዛሬና አሁን በተራ የመንደር ጉሊት ገብቶ ግማሽ ኪሎ
ቲማቲምና የሁለት ብር በቁጥር ሦስት ወይ አራት የሚሆን ቃሪያ ከጥቂት ቀይ ሽንኩርትና አንድ
የጠወለገ ሎሚ በመግዛት(አንድ ሎሚ እንኳን ሁለት ብር ሲገባ?) ሰላጣ ሠርቶ የሚበላበት ዱዲ የሌለው
ሙልጭ የወጣ ድሃ ሆኗል(የአለባበሱ ነገርማ አይነሣ!)፡፡ ያኔ በሃምሳ ሳንቲም ‹ከዚህ መልስ ቁረጥልኝ›
እያለ ቤተሰቡን በሥጋ ያሰለች የነበረው ንዑስ ከበርቴ ዛሬ የቲማቲም ቁርጥ ብርቅ ሆኖበት ስታዩት
አለመፈጠሩን ትመኙለታላችሁ፡፡ ያኔ የአንድ ወር ደመወዙን አብቃቅቶ መላዋን ኢትዮጵያ ሊጎበኝ ይችል
የነበረው ንዑስ ከበርቴ ዛሬ የወር ደመወዙ እንኳንስ ሀገር ሊያስጎበኘው ከደረጃ በታች የሆነ የጥቁር ጤፍ
እንጀራ በእንደነገሩ የሽሮ ወጥ በልቶም ከወር እወር ሊያደርሰው አልቻለም፡፡ ትልቁ የሀገርና የማኅበረሰብ
ኪሣራ ደግሞ በሚገኝ የወር ገቢ ቢያንስ ከወር እወር መድረስ አለመቻል ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን መረገም
ግዘፍ ነስቶ የጭራቅን ያህል አስፈሪ ሆኖ የታየበት ብቸኛው ዘመን ይህ የኛው ዘመን ነው፡፡ እርግማኔን
ጀመርኩ - ወያኔዎች ጥቁር ውሻ ይውለዱ!!
ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሸልለህ ለመኖር ያለህ ምርጫ አንድ ነው - ኢትዮጵያንና
ኢትዮጵያዊነትን መካድ - በቃ፡፡ ያኔ ዘንጠህ ትኖራለህ - ተንደላቅቀህ፡፡ ኢትዮጵያዊነትህን በካድህ ማግስት
ሁሉም ማቴሪያላዊ ችግሮችህ ተጠራርገው ከነሰንኮፋቸው ይነቀሉልሃል፡፡ ያኔ ታዲያ ኅሊና የሚባለው
አመዛዛኝ ፍጡር ሊኖርህ በጭራሽ አይገባም፡፡ ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻልህምና አንዱን መምረጥ
ይኖርብሃል፡፡ ኅሊናህን መጠቀም ከፈለግህ ድህነትን መምረጥ ሊኖርብህ ነው፤ ባለጠግነትን መምረጥ
ከፈለግህ አቅልህን ስተህ ቀልብህን ወደቁሣዊ አብረቅራቂው ዓለም ሰብሰብ በማድረግ ቀን ከሌት ገንዘብ
ሊገኝ የሚችልበትን መንገድ ማውጠንጠን ነው፡፡ እሱም ቀላል ነው፡፡ በዚህ ሂደት እንደነገርኩህ ወያኔ
መሆን ከሁሉም መንገዶች የመጨረሻው ቀላል መንገድ ነው፡፡ በዚያ መንደር አእምሮ እንጂ ሀብት በሽበሽ
ነው፤ ጤንነት እንጂ መብልና መጠጥ እንደጉድ ነው፡፡ ፍቅር እንጂ ጥላቻና ይሉኝታቢስነት እንደልብ
ነው፡፡
ወያኔ ሁንና ወይም የወያኔን የአጥፍቶ መጥፋት ፖሊሲ ደግፍና ወደንግዱ ሰተት ብለህ ግባ፡፡
በአንድ ቀን አዳር ትከብራለህ፡፡ አንድም ባለሥልጣን - እደግመዋለሁ - አንድም ባለሥልጣን ለሀገርና
ለወገን የሚጨነቅ የለም፤ የሚጨነቅ ከሆነ የሲስተሙን -የሥርዓቱን ማለት ነው - ፍሰት ስለሚያጨናጉል
በአፋጣኝ እንዲወገድ ይደረጋልና በዚህ አባባሌ ቅር የሚለው ሰው እንዳይኖር አደራየ የጠበቀ ነው፡፡
በቆሻሻ ቱቦ ውስጥ በአጋጣሚም ይሁን በሌላ መንገድ የሚገኝ ንጹሕ ነገር ያለው አማራጭ ሁለት ብቻ
ነው - አንድም ከቆሻሻው ጋር አብሮ ቆሻሻ መሆን አንድም ተለይቶ መውጣት፡፡ ስለዚህ በወያኔ ውስጥ
ሆኖ ንጹሕ ነኝ ማለት መፀዳጃ ቤት ውስጥ ተቀምጦ ፈስ ገማኝ እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዐዋጁ የጸና ነው
- ‹በወያኔ ውስጥ የሚገኝ ባለሥልጣን ሁሉ ቆሻሻ ነው› - ቢያንስ እስኪጣራ እንኳን ‹ቆሻሻ› ነው›፡፡
እያንዳንዱ ባለሥልጣንና ካድሬ በሙስና ኃጢያት ያመነዘረ ወይም ከአመንዝራዎች ጋር የተባበረ በመሆኑ
ለንስሐ ሕፅበት መትጋት ያለበት ኃጥዕ ወአባሲ ነው - በቃ! እየተዋወቅን?
ስለዚህ ከቆሻሻዎቹ ባለሥልጣናት ጋር እየተመሳጠርክ በንግድና በልዩ ልዩ ሙስና ውስጥ መዘፈቅና
በአንዴ መክበር ወያኔያዊ መብትህ ነው፡፡ የመክበሪያ ቁልፍ ግን ከፍ ሲል እንደተናገርኩት ኅሊናቢስነት
ነው፡፡ ኅሊናህን ሆድህ ውስጥ ሸጉጠህ ተመሳስለህ መኖር ነው፡፡ ሃቲማህ ግን አያምርም፡፡
ኅሊናቢስነት በምን በምን ይገለጻል?
ባለሥልጣንና ካድሬ ከሆንክ የመንግሥትንና የሕዝብን ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት ባወጣልህ ዋጋ
መቸብቸብ ነው፡፡ እንደየሥልጣንህ ተዋረድ ገንዘቡ አንድም በቦርሣ ታጭቆ በፈለግኸው ቦታ
ይመጣልሃል፤ አሊያም በፈለግኸው ዓለም አቀፍ ባንክ በስምህ ይገባልሃል - ዕድሜ ከሰጠህ ትበላዋለህ -
ባጭር ከተቀጨህም አይዞህ በይ አይጠፋም - ቢያንስ ጎባንህ ያልፍለታል፡፡ ለጊዜው ግን የመኖሪያ ቤት
መሥሪያ ኪስ ቦታዎችን በቃፊሮችህ እያፈላለግህ ለኢንቬስተርና ለዲያስፖራ በመሸጥ፣ ከነጋዴዎች ጋር
በሚደረግ ግልጽም ሆነ ሥውር መመሳጠር ከፍተኛ ጉቦ በመቀበል፣ የመንግሥትን ሀብትና ንብረት ‹ሌላ
ዘዴ ከተገኘ በጨረታው አንገደድም› በምትለዋ ቀጣፊ አንቀጽ ሰበብ በሙስና በርካሽ ዋጋ በመሸጥ፣
ገበሬዎችንና ነባር ነዋሪዎችን እያፈናቀሉ የሀገርንና የወገንን መሬት ለውጭና ለሀገር ውስጥ ባለሀብት
ባወጣ በመቸርቸር፣ ስንቱ ተነግሮ ... በነዚህ ሁሉ መንገዶች መክበር ቀላል ነው፡፡ እያየነው? ወያኔዎች
ግን ጥቁር ውሻ ይውለዱ!!
መክበሩ ይሁን፡፡ ማንም በምንም መንገድ ይክበር፡፡ ኋላ የሚያልፍበት ራሱ ነው፡፡ ነገር ግን የሕዝብ
ኑሮ እንዲህ ሰማይ እንዲደርስ የሚደረገው ለምንድነው? ለምን የግፍ ግፍ ይሠራል? ጥቂቶች እየኖሩ
ሚሊዮኖች በቀን አንዴ እንኳ እንዳይመገቡ የሚደረገው ለምንድነው? ዜጎችን አልልም - ዜጋን በዜግነቱ
የሚቀበል መንግሥትም ሆነ የመንግሥት አካል ስለሌለ፤ ነገር ግን ሰዎችን በማስራብ የሚገኝ ደስታ ምን
ዓይነት ደስታ ይሆን? የዚህ ሁሉ የሕዝብ ሥቃይ የሚያመጣው የዞረ ድምር እንዴት አልታየም?
በእውነቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን እየኖረ ነውን? ሆድ ሲጠግብ አንጎል በሞራ የሚሸፈነው ለምን ይሆን?
ሥነ ቃላችን እንደሚለው ከተራበ ለጠገበ መታዘኑ ለዚህ ይሆን?
ደመወዝና ኑሮ ቻው ቻው ከተባባሉ ቆይተዋል፡፡ በደመወዝ መኖር የሚችል ዓለም አቀፍ ደረጃ
የደመወዝ ክፍያን በሚከተሉ ተቋማት አንጂ በሲፒኤ ተብዬው የኢትዮጵያ መንግሥት የደመወዝ እስኬል
የሚከፈል ሠራተኛ እስትንፋሱ ተንጠልጥላ የምትገኘው በተራድዖና በልዩ ልዩ ድጎማ ነው፡፡ ልጁን
ወደዐረብ ሀገርና ወደሌላው ዓለም የላከ፣ በደህናው ዘመን የሠራትን ጎጆ እየሸጠና እየለወጠ ላለመሞት
የሚንደፋደፍ፣ በደጉ ዘመን በሠራት ቤቱ የሚከራይና ለሱቅ የሚሆን ቤት ያለው፣ በትርፍ ሰዓቱ
አለባበሱንና ገጽታውን ለዋውጦ በልመና ‹ሙያ› የተሠማራ፣ አሁንም በትርፍ ሰዓቱ ሥርቆትን ጨምሮ
ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ‹ሥራዎች› ላይ የተጠመደ... የዛሬ ነፍሱን ለነገ ያደርሳል፡፡ አለበለዚያ እመኑኝ
በመንግሥት ደመወዝ እንኳንስ 30 ቀናትን ለመቆየት ይቅርና 3 ቀናትም ይከብዳሉ፡፡ ምን ተበልቶ? በምን
ተጉዞ? ምን ተለብሶ? በምን ታክሞ? ለማንኛውም ወያኔዎች ጥቁር ውሻ ይውለዱ!!
ሀኪሙ ሌባ፣ ሆስፒታሉ ሁላ ሌባ፣ ዶክተሩ አጭበርባሪ፣ ፖሊሱ ሌባ፣ ዳኛው ሌባ፣ ጠበቃው ሌባ፣
ዐቃቤ ሕጉ ሌባ፣ ወታደሩ ሌባ፣ መንግሥቱ ማፊያ፣ ባለሥልጣኑ ሌባ፣ ነጋዴው ሌባ፣ ሲቪል ሰርቫንቱ
እጅ እጅህን የሚያይ ሌባ፣ ቀበሌው ሌባ፣ ... ሁሉም ሌባ በሆነባት ሀገር እንዴት መኖር ይቻላል?
እንዴ! ለእግርህ ወለምታ ወደ አንድ የግል ሕክምና ተቋም ብትሄድ ካርዱ አምስት መቶ ብር ይሆንና
ጭንቅላትህ ራጅ ይነሳ፣ አክታህ ይመርመር፣ እርግዝናህ እግርህን ሊኮደኩደው ስለሚችል ሽንትህ
ይመርመር፣ የአንጀትህ መታጠፍ ለእግር ወለምታ መቀስቀስ ሰበብ ሊሆን ስለሚችል በአልትራሳውንድ
ውስጠ ዕቃህ ይታይ፣ በሲቲ ስካን ሁለመናህ ይፈተሸ፣ 11 ዓይነት የደም ምርመራ ይደረግልህ ...
የማትባለው እኮ የለም - ለወለምታ፡፡ ኤቲክስ፣ ሞራል፣ ሃይማኖት፣ ይሉኝታ፣ግዛዕ ምዛ የለም፡፡ ሆድ ነው
ንጉሠ ነገሥቱ በሀገራችን፡፡
የግል ሆስፒታል አልጋ ከሼራተንና ሒልተን አልጋ በልጦ ብታገኘው እንዳይደንቅህ - ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የምትገኘው፡፡ አብዛኛው ሰው የለየለት ጅብና ዓሣማ ሆኖ ዐረፈው፡፡ ምን ይሆን ግን ወደዚህ የለየለት ሀገራዊ ቀውስ ውስጥ የዘፈቀን? በነገራችን ላይ ከንፍሮ ጥሬ አይታጣምና ምናልባት በዚህ አንቀጽም ሆነ በቀደሙትና በሚለጥቁት አንቀጾች ከምለው ነገር ነጻ ልትሆኑ የምትችሉ ዜጎች ካላችሁ መሬት ላይ ወድቄ ይቅርታችሁን እለምናለሁና ይቅር በሉኝ፡፡ ወድጄን እንዳይመስላችሁ፡፡ ግን ግን አሁንም ወያኔዎች ጥቁር ውሻ ይውለዱ!!
ነጋዴው ጨርቁን ጥሎ አብዷል፡፡ በገንዘብ ፍቅር ናላው ዞሯል፡፡ በገንዘብ ብቻም አይደለም፡፡
በሀገራችን ብዙው ሰው በሥልጣን ፍቅር ቅንጭላቱ ናውዟል(እንዲያ ባይሆን ኖሮ መቶ ታምሳ ፓርቲና
የፖለቲካ ድርጅት በውጪም ባገር ውስጥም ይኖር ነበር? - በሬው ሳይገዛ ሌባው በረት ሞላ አሉ!
አለመታደል ነው!)፤ ብዙ ሰው በፍቅረ ንዋይ ታውሯል፤ በወሲብ አራራም አቅሉን የሳተው የትዬለሌ ነው፡
፡ በአዲስ አበባ ሥሪያውን ያያችሁ እንደሆነ ‹እንዴ፣ ዓለም የምታልፍበት ቀን በቁርጥ ተነገረ እንዴ?›
ብላችሁ ልትገረሙ ትችላላችሁ፡፡ የሃይማኖት መላላትና የማኅበረሰብኣዊ ዕሤቶች ደብዛ መጥፋት ምን
ዓይነት ሀገራዊ ቀውስና የትውልድ ዝቅጠት ሊያስከትል እንደሚችል እኛን ያየ ታዛቢ በቀላሉ ይረዳል፡፡
በቁማችን መሞታችንን ለመታዘብ አዲስ አበባ መምጣትና በቀንና በሌሊት የሚሠሩ ሰይጣናዊ
ድርጊቶችንና በተቃራኒው ደግሞ የአብዛኛውን ሕዝብ የርሀብ ሰቆቃ፣ የዜጎችን የለየለት ዕብደትና ለብቻ
እየተናገሩ እንደወፈፌ ሲጓዙ ማየት በቂ ነው - ዛሬ ካበደው ደግሞ ነገ ለማበድ የተዘጋጀው ይበልጣል፡፡
የሶዶምና ገሞራ የዕልቂት ዘመን በጣም ተቃርቧል ብዬ ለማመን የተገደድኩበት ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት
እችላለሁ - እንደ አካሄድ፡፡ የቀረን የፊሽካው መነፋት ብቻ ይመስለኛል፡፡
ነጋዴዎች በኪሎ ይሸቅቡሃል፤ ጥራት የጎደለው ብቻ ሳይሆን ለጤንነት ፀር የሆነ የምግብና ምብግ
ነክ ሸቀጦችን ያቀርቡልሃል፤ሱስ እንዲይዝህ በሻይ ቅጠል ሳይቀር ትምባሆ ጨምረው ያሽጉልህና
ሲያስፋሽግህ እንዲውል ያደርጉሃል፤ በመጠጦችም ውስጥ ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገሮችን እየጨመሩ
መሸተኛ ሆነህ እንድትቀርና በሰበቡም ቤተሰብህን እንድትበትን ያደርጉሃል፤ ሦስት ቀን ለማያገለግሉ
የቻይና ትርኪ ምርኪ ሸቀጦች ያጋልጡሃል - ከገንዘብህም ከዕቃውም ላትሆን፤ ሰውነትህን ለሚኮደኩድ
የየመን ስምየለሽ የመብል ዘይት ያጋልጡሃል፤ ለሆነ ጉዳይህ አሥር ኪሎ ብለህ የገዛኸው ሥጋ የኪሎ
ሚዛኑ ሰባት ሆኖ በዚያም ላይ አጥንትና ልፋጭ አሸክመው ቢልኩህ ብቸኛው ምርጫህ ከሚስትህ ጋር
እቤትህ ሀዘን መቀመጥ ነው፡፡ ሸክላና ሴጋቱራ ከመናኛ የበርበሬ ዛላ ጋር ፈጭተው በበርበሬ ስም
ቢያበሉህ ለጤንነትህ አንድዬን ብቻ መለመን ነው፡፡ ከሥነ ልቦናህና ከባህልህ ከምግብ ሥርዓትህም
ያልተለማመዱ የቤትና የዱር እንስሳትን አርደው ሊመግቡህ ቢችሉ መታገስ ነው፡፡ የበከተ ዶሮና ከብትማ
የዘወትር ቀለብህ ነው - ዶሮ ወይ በግ ሳትታረድ ሞተች ብሎ መጣል ታሪክ ሆኗል ልጄ - አከፋፋይና
ተቀባይ አላቸው፡፡ ዘይቱ፣ ቅቤው ከምን እንደሚሠራ አታውቅም - ያን እየተመገብክ የቀብርህን ጊዜ
ማሣጠር ነው፡፡ ጤፉን ግማሽ በግማሽ ከአሸዋና አፈር ቢቀላቅሉት ነፍተህ መጠቀም እንጂ ቅሬታ
ማሰማት በሞኝነት ያስፈርጅሃል፡፡ ብዙ ነገር ከመስመር ወጥቷል፡፡ ነጋዴው የሚታየው ብቸኛ ነገር ገንዘብ
እንጂ ሌላ አይደለም፤ ብዙው ነጋዴ ከሰውነት ተራ ወጥቶ ገንዘብን አምላኪ ሆኗል - ከጣዖትነት በዘለለ
ሁኔታ፡፡ በጥቀሉ ያልሆንነው የለም፡፡ ‹ብታምኑም ባታምኑም ወያኔ ቀልዶብናል› ነበር ያለው መንግሥቱ
ኃ/ማርያም? የሥራቸውን ይስጣቸው እንጂ ነጋዴዎችና ወያኔዎች ቀልደውብናል፡፡ አንድዬ ዋጋቸውን
አይነሳቸው፡፡
የኑሮው ልዩነት አይወራም፡፡ ስንትና ስንት ቤተሰብ የቀድሞ የነተበ ሱፉን ከነክራቫቱ ግጥም
አድርጎ ከሆቴሎች የተሰባሰበ - ወጣቶች ቱሩ ይሉታል - ትርፍራፊ በቅናሽ ዋጋ ለመግዛት ከ‹አከፋፋዮች›
ደጅ ተሰልፎ ስታዩት ልታለቅሱ ትችላላችሁ፡፡ ትራፊን ለውሻ ማከራየት ዱሮ ቀረ፤ አሁን ‹ዛሬ ከምሞት
ነገ ልሙት› ከሚል የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ የተነሣ ያ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ዕድሜ ለወያኔ ክብሩን
አዋርዶ ለሆቴል ትራፊ መሰለፍ ከጀመረ ዋል አደር አለ - ይሄው ትራፊ በጉርሻ ደረጃም ይሸጣል -
ያም እየጠፋ ነው፤ ኩራት እራት የሚሆነው የሚንጫጫ ወስፋት ሳይኖር ነው - እዬዬም ሲደላ ነውና፡፡
ወያኔዎች ጥቁር ውሻ ይውለዱ!!
ልመናውና ዘረፋው ቀልጧል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች የቀን ዘረፋም እንደተጀመረ ይነገራል፡፡
በዘረፋውም የፖሊስ ኃይሉ አባላት እንደሚተባበሩበት እንሰማለን - እነሱስ ማን አላቸው? በሰባት መቶ
ብር ደመወዝ እንዴት ይኑሩ? ይሄም ብቻ አይደለም - በ12 ብር ሒሳብ አራት ኪሎ ሙዝ የሚገዛ
የጡረታ አበል የሚከፈልባት ደናቁርት የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚገኙባት ብቸኛ የዓለም ሀገር
ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ ወፍራም የምትሉት የመንግሥት ደሞዝ በሙስና ወይም በሌላ መንገድ ካልተደጎመ
አያኖርም፡፡ ... የኔ የወንድማችሁ ደመወዝ - የእህታችሁ ብልም ግዴለኝም - (ውኃን ለመክፈልና ጥቂት
ኩታራዎችን ከማፍራት ውጪ ምን ጠቀመኝ? የተጠቀሙበትስ ባሉበት አሉ! መንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት
ሕንፃ ላይ ሳይቀር ገትረውት የለም እንዴ! ግን እኮ በዚያ ቦታ ነውር መሆን ነበረበት፤ በክርስቶስ ቦታ
የወንድነትን ልክ ማሳያ ጥንታዊ ሀውልት ሳይሆን የላሊበላው የመስቀል ምልክት ቢሆን ይሻል ነበር፤
መሃንዲሱ አክሱማዊ መሆን አለበት! ) - የኔ የ‹ንዑስ ከበርቴ›ው ወርኃዊ የተጣራ ደመወዝ ከባለቤቴ
ወይም ከአንድ ጓደኛየ ጋር ኪሎውን በ150 ሒሳብ በወር ሃያ ጊዜ(20ኪ.ግ) ጥብስ ወይም ቁርጥ ከማብላት
አያልፍም - ሻይና ማወራረጃ አምቦ ወይ ለስላሳ እንኳን ሳይጨምር፡፡ ሕዝብ በፍትህ ዕጦት ብቻ ሳይሆን
በርሀብም እያለቀ ነው፡፡ ወያኔዎችም ግፍን በግፍ ላይ እየቆለሉ የራሳቸውን ጉድጓድ አርቀው እየቆፈሩ
ናቸው - ምን ቸገረን - ይቆፍሩ፡፡ እርግማኔን ግን እቀጥላለሁ፤ እናም ልጅ አይውጣላቸው!! እስከዚህ
እንዳዋረዱን ሳያስቡት በላ ይላክባቸው!! ዕጣቸው ጥርስ ማፋጨትና በሲዖል የዕቶን እሳት መለብለብ
ይሁን፡፡
ኢትዮጵያ ስሟ ያጸይፋል እንዴ?
ነገርን ቢዘበዝቡት አያልቅም፡፡ ከፍ ሲል በጅምር ወደተዉኳት በመሀል የተሸረጠች ሃሳብ ልግባና
ቁጭቴን ልቋጭ፡፡ ሆድ ለባሰው ማጭድህን አውሰው ይባላል- (ሳላውቅ አዟዟርሁት ልበል?)፡፡ አሁንስ
ከሆድም አልፎ አንጀትም ብሶኛል፡፡
ባለቤቴ ‹ደገሙልህ!› አልነበር ያለችኝ? አዎ፣ እንዲያ ነበር ያለችኝ፤ የደገሙት ኢሣቶች ናቸው፤
ዛሬ ጧት ለአራተኛ ጊዜ የደገሙትም(ማለትም ያቀረቡት) ትናንት ለሦስት ጊዜያት ያህል በአንድ ቀን
ጀምበር ለአየር ያበቁትን ከአንዱፌ ጅራ(ዳዊት መኮንን) ጋር ያደረጉትን ግሩም ቃለ መጠይቅ ነው፡፡
‹እንዴት ነው ኖገሩ? ለአንድ ሞቶ ሃምሣ ብር ከፍዬ ከዐረብሣት ወደናይልሣት የጎለበጥኩት ለዚሁ ነው
እንዴ?› አይ፣ ግዴላችሁም ይስተካከል፡፡ በፓርትታይም እየተሠራ ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለውጥ የሕይወት
ቅመም ነውና አቀራረቡ ለወጥወጥ ማለት አለበት፡፡ በመሠረቱ ብዙ ነገሮች ጥሩ ናቸው፡፡ ከፍተኛ
መሻሻልም እየታዬ ነው፡፡ ግን ግን አሁንም ብዙ ይቀራል፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ዲያስፖራ ቢያንስ
አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀጥ አድርጎ መያዝ ካቃተው አሳፋሪ ነገር ይመስለኛል - የኛን የብዙኃኑን ያገር
ቤት ዜጎች ነገር ተውት፤ ከሞቱትም ካሉትም በታች ሆነናልና የኛ ጉዳይ ተከድኖ ይብሰል፡፡ ብል
ለሚበላው ሀብትና የዓለም ንብረት እጅን ማሳጠር ደግ አይደለም፡፡ የኢሣት ሰዎችም ብቻቸውን
እንዲፍጨረጨሩ መተው የለባቸውም፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ ለጥቂቶች ብቻ እንደፍጥርጥራቸው ይወጡት
ተብሎ የሚተው ነገር አይደለም፡፡ ነገ እንተዛዘባለን፡፡ በእርግጠኝነት ነጻነታችን በባሌም ይሁን በቦሌ
መምጣቱ አይቀርም፡፡ ያኔ ሀገራችን ‹አላውቃችሁም› ብትለን ምን ይውጠናል? የክርስቶስን አስተምህሮ
አስታውሱ፡፡ ‹ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማይ አይገባም› ያለው ምንን ሊያስተምር
እንደሆነ አንዘንጋ፡፡ እየቻልን ሀገራችንን ከረሳን ነውር ነው፡፡ ሁሉም ከተባበረ ኢሣት የሚወቀስባቸውን
ቀዳዳ ጎኖች ለመድፈን አያቅተውም፡፡ አንራቀው - እንቅረበው፡፡ ጦራችን ነው፤ የሕዝብ አለኝታ ነው፡፡
ኢሣት የወቅቱ የጭቁኖች እስትንፋስ ነው፡፡ እርግጥ ነው - በሁለገብ ትግል ካልታገዘ ቲቪም ሆነ
ማንኛውም ሚዲያ ብቻውን ነጻነትን ያመጣል ማለትም አይደለም፡፡ ስለዚህ ሀቀኛ ኢትዮጵያውያን
ልዩነቶቻቸውን ጋብ አድርገው አዲስ ታሪክ መሥራት ይገባቸዋል - በየፈርጁ፡፡ እግዚአብሔር የኛን
ጦርነት አይዋጋም - እንዲዋጋልን መጠበቅም የዋህነት ነው፤ ምክንያት ፈጥሮ ግን ሀገርንና ሕዝብን
ከጨቋኝ ሥርዓት ሊታደግ እንደሚችል የታወቀ ነው - ዕቅዱን ማፋጠን የሚቻለን ይመስለኛል፤ ‹አንኳኩ
ይከፈትላችኋል› አለ እንጂ እደጅ ቆማችሁ አላዝኑ ወይ አንቀላፉ አላለምና እንወቅበት፡፡... በደረቅ አበሳ
እርጥብ ይቃጠላል፡፡ ለኃጥኣን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል፤ ለጻድቃን የመጣም ለኃጥኣን ይተርፋል፡፡ የሆኖ
ሆኖ ወያኔዎች ጥቁር ውሻ ይውለዱ!!
ያን ቃለ መጠይቅ በተመለከተ ግን የተሰማኝን ቅሬታ ሳልጠቁም ማለፍ አልወድም፡፡ ይሉኝታ ዱሮ
ቀረ ምዕመናን፡፡ ጫካ አይደለሁምና የተሰማኝን እናገራለሁ - የፈለገ ይውሰደው ያልፈለገ ይተወው፤
ገበያና ንግግር የጋራ ነው - የስምምነት ጉዳይ ነው፡፡ እና ዳዊት መኮንን እጅግ የሚመስጥ ቃለ መጠይቅ
የማድረጉን ያህል በዚያ ሰፊ ንግግሩ ውስጥ ተስቶት እንኳን አንድም ጊዜ ‹ኢትዮጵያ› የሚል ቃል
አለመናገሩን ሳጤን በጣም ከፋኝ - ይህን ጽሑፍ ከጀመርኩ በኋላ አንድ ከጉራጌ ብሔረሰብ የሚወለድ
ጓደኛየ ይህን የኔን ትዝብት ራሱ አስታውሶኝ ቅር እንዳለው ሲያጫውተኝ በኢትዮጵያዊነታችን የጸናን ነን
የምንል ምዝብር ዜጎች ምን ያህል የአእምሮ መናበብ እንዳለን ተገነዘብኩ - ይቅርታ ሰውን በዘር ቋጠሮ
መለያየትና መናገርም አልወድም - በመሠረቱ - ነገር ግን እዚህ ላይ አስፈላጊ ሆኖ በማግኘቴ ነው፡፡
ኢትዮጵያን መጥላት የማንም መብት ነው፡፡ ይሁንና የዚህ አርቲስት ‹ኦሮሚያ› ላይ ማጥበቅና ኢትዮጵያን
ገሸሽ ማድረግ በአብሮነታችን ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ሳስበው ልጁ ያልገባው ነገር እንዳለ ተረዳሁ፡፡
በኋላ የወጣ ቀንድ በፊት የወጣ ጆሮን ጣል ጣል ማድረግ እንደማይኖርበትም ላስታውስ ፈለግሁ፡፡
ከ22 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ባንዲራና አንዲት ሉዓላዊት ሀገር ከአንድ ሕዝብና
ከአንድ መንግሥት ጋር ነበሩ - ምንም እንኳን መንግሥታቱ ጨቋኝና አምባገነን ቢሆኑም - ስትፈልጉ
ዘውድ ናፋቂ ወይም ደርግ ኢሠፓ በሉኝ (ሁለቱንም እንዳልሆንኩ የማሳወቅ መብቴ ግን ባልተሸራረፈ
መልኩ እንደተጠበቀ ነው)፡፡ ወያኔ ለዘዴዋ ስትል ሠላሣ ባንዲራና እውናዊ ኅልውናቸው ከላም አለኝ
በሰማይ ያልዘለሉ ሠላሣ ክልላዊ መንግሥታት ፈጠረችና ለየዋሃን አደለች፡፡ የዋሃን ያን የመከፋፈያ
ሥልት እንዳለ ተቀብለው ይንከረፈፉ ገቡ፡፡ እሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል እንዲሉ ከደደቢት - ትግራይ
ሲገሰግስ የመጣው የመለስ ዜናዊ የጥፋት ሠራዊት ለሕዝብ ያዘነ መስሎ የዐዞ ዕንባ እያነባ ሀገሪቱን በዘርና
በቋንቋ ተልትሎ ራሱ ለጠፈጠፋቸውና ቀድመው ለተፈጠሩ ተቃዋሚዎች የባንዲራ መዓት በማደል
በውስጡ እዬሣቀ የልቡን ይሠራ ያዘ - ከእውነት ያታለለ መስሎት(በመንጌ አማርኛ - ብታምኑም
ባታምኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኒት ለቅጣት እንደመጣች ጠንቅቆ ያውቃልና ማንንም ሊያታልሉ
አይችሉም!)፡፡ ሁለገብ ሟርትና ደንቃራው ይዞለት ዋናው የሠራዊተ አጋንንት መሪ መለስ ዜናዊ በቃህ
ተብሎ በአምላከ ኢትዮጵያ እስኪጠራ ድረስ ትርምሱና ዋይታው በርትቶ ቀጠለ - አሁን ድረስ፡፡...
ይህ ትውልድ ከሸፍጥና ሸፍጠኞች ካጠመዱለት ቀረቀር በአፋጣኝ ካልወጣ የጉዳቱ ሰለባ ራሱ
እንጂ ሌላ ማንም አይሆንም፡፡ አንድን ችግር ለማስወገድ ችግሩ የተፈጠረበትን የአስተሳሰብ ጎዳና መከተል
እንደማያዋጣ አልበርት አነስታይን አስቀድሞ ተናግሯል - የክርስቶስ ስብከተ ፍቅር ‹ጠላትህን ውደድ›ም
ከዚህ የተለዬ አይደለም፡፡ ችግሩ ከተፈጠረበት አእምሮ የበለጠና የሰላ አእምሮ ባለቤት መሆንን ይጠይቃል
- ተፈጠረ የተባለን ችግር በማያዳግም ሁኔታ ለመፍታት፡፡ እናም ወያኔ በተጓዘበት መንገድ ተጉዞ
የሕዝብን ነጻነት አመጣለሁ ማለት ዘበት ነው - ወደትፋቱ እንደሚመለስ እሪያ(ዓሣማ) መሆንም ነው፤
አንገት ለምን ተፈጠረ - አዙሮ ለማየት አይደለምን? መቶ ሃምሳው ተቃዋሚ በመቶ ሃምሳ ባንዲራና
ሰንደቅ ሥር ተሰልፎ ቢመጣ ቂልነት እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡ በሌላ በኩልም ዘመደ ብዙ ጠላው
ቀጭን እንደሚሆንበት በመረዳት ለማያዋጡ አካሄዶች ከማጎንበስና ጥቁርና ነጭን ተቀላቅለው ላይቀላቀሉ
ለማቀላቀል በመሞከር በቡራቡሬ ግንጥል ጌጥም ለመዋብ ከመድከም ይልቅ የሚያዛልቁ አካሄዶች ላይ
መላ ትኩረትን ጥሎ ለትዝብት በሚዳርግ ሁኔታ ሳይንጋለሉ አዋጪውን ልጅ ብቻ በመምረጥ ማጥባትን
መለማመድ ክፋት ያለው አይመስለኝም - በዚህች ዐረፍተ ነገር ምን ለማለት እንደፈለግሁ ለኔ ለራሴ
ላቲን ሆኖብኛልና የገባው ወደፊት ቢያስረዳኝ ደስ ይለኛል - አልሰርዛትም ደግሞ፡፡ ... ስለሆነም ወደ
እውነቱ መቅረብ ያስፈልጋል፡፡ አዳሜ በየብሔሩና በየጎሣው እየተመሰገ በመጤ ባንዲራና በፍልሱፍ
ማንነት ሕዝብን ሊያታልል ቢሞክር ዕድሜው ብዙ አይደለም፤[ ሰውን ግን ምን እየነካው ነው? ባንዲራን
ያህል ትልቅ ነገር በቤተ ሙከራ ፈልስፎ የቡና ቁርስ ይመስል እንዴት ለሕዝብ ያድላል? ወያኔዎች እኔ
ለተገኘሁበት የሕዝብ ክፍልም የፈለሰፉት ባንዲራና ብሔራዊ የማንነት መገለጫ አለ አሉኝ - ግን
ሁለቱንም አላውቃቸውም፤ ማንነቴ ኢትዮጵያዊነቴ - ባንዲራየም የሰይጣን ዓርማ የሌለበቱ ንጹሑ
አረንጓዴ - ቢጫ - ቀይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚያኮራ ማንነት እንጂ የሚያሣፍር አይደለም፡፡ በጊዜ
እንመለስ ጎበዝ!]
በተረቱ ‹የሞኝ ፍልጥ ካላንድ ቀን አይበልጥ› ይባላልና አሁን ለጊዜው ሕዝቡ አማራጭ አጥቶ
ከላይ የተወረወረው ቁዝምዝም መሬት እስኪያርፍለት ዝም ስላለ ብቻ ለዕልቂትና ውድመት የሚዳርግን
የመሠሪዎች ሸቀጥ የዘር ፖለቲካ ከእንግዲህ ወዲያ ይቀበላል ማለት እንዳልሆነ ሁላችን ልንገነዘብ ይገባል
- ቋቅ እስኪለንና እስኪያንገሸግሸን አየነውም አይደል? ማንን ጠቀመ? ማንንስ እንጦርጦስ አወረደ?
በመሠረቱ ይህን ወይ ያን መጥላት ይኖራል፡፡ በተቀያየምክ ቁጥር ወይም የጓደኛህ የ‹ዐይን ቀለም›
ባስጠላህ ቁጥር ግን ከሜዳ ተነስተህ በሞቅታም ይሁን በለብታ የጋራ ቤትን ሊያርስ የሚችል የተለዬ
ነገር አታደርግም፡፡ ባሏን የጎዳች መስሏት ሰውነቷን በእንጨት እንደቦጫጨረችው ቂላቂል ሴት ለመሆን
እስካልተፈለገ ድረስ የበሬ ግምባር በማታህል ሀገር ሰማንያ ባንዲራና ሰማንያ ማንነት ለማቆጥቆጥና
ሕዝብን ለማወናበድ መነሳት በተለይ ከአሁን ወዲያ አያዋጣም ብቻ ሳይሆን የለየለት ጅልነት ነው፡፡ ሊሣካ
ቢችል ኖሮ እስካሁን ነበር የሚሳካው፡፡ ባጭሩ አይሆንም ነው - የሚወጣና የማይወጣ እንጀራ ከምጣዱ
ያስታውቃል፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ በቅርቡ ሁሉንም ነገር ‹አፖስቶ› ያደርገዋል የሚል ሥጋዊ ግምትና
መንፈሳዊ ጠንካራ እምነት አለኝ - ያስተካክለዋል ማለቴ ነው በሶላቶኛ፡፡ አሁን ማን ይሙት በሰው
ኃይልና በመንግሥት ጥበቃ የምንኖር ይመስላችኋል? አይደለም! በኪነ ጥበቡ ነው እየኖርን ያለን -
መንግሥት ለስሙ - ጠ/ሚንስትር ለስሙ - ፖሊስ ለስሙ - ጤንነት ለስሙ ... ሁሉም ለስሙ እንጂ
ከእውነት የለንም፡፡ አንዱ ገድሎህ ቢሄድ ዋስትና የለህም፡፡ አውላላ ሜዳ ላይ ያለ እረኛ የተበተነ ከ80 –
90 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ! አዲስ ታሪክ፣ አዲስ ዓለማቀፋዊ ኹነት! የሚገርም ሕይወት እኮ ነው
እየመራን ያለነው በውነቱ!
ይህን ጉዳይ ለብቻው ብመለስበት ይሻለኛል፡፡ ለዛሬ ጣፈጠም መረረም እዚህ ላይ ላብቃ፡፡ አጎቴ
አባ ዘባሪቆ እንዲህ ይሉ ነበር - እጠቅሳለሁ፡- አንድ ጽሑፍ የምትፈልገውንም የማትፈልገውንም
የምታገኝበት ብፌ ማለት ነው፡፡ የማትፈልገው የምትፈልገውን እንዳያጠይምብህ በአስተውሎት አንብብ፡፡
ሁሉን ማስደሰት የሚቻለው አንድም ፍጡር የለም፤ ፍቅር ግን ቻይና ታጋሽ ናት፡፡ ከችኩል ፍርድ
ተቆጠብ፡፡ ልዩነትን ‘enjoy’ ማድረግ ያልለመደ ሰው፣ ሰው ሳይሆን ያረጅና እንደፊጋ በሬ ዙሪያ ገባውን
በነገር ቀንዱ እንደደሰቀና ከሁሉም ጋር እንደተጣላ ሰው ሳይሆን ያልፋል፡፡ የጥቅሱ መጨረሻ፡፡ “ይህን
ጽሑፍ ያነበበ፣ ያስነበበና ያናበበ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡” ብል በ‹plagiarism› እከሰስ ይሆን?
ለማንኛውም እርግማኔን ሳልረሳው “ወያኔ ጥቁር ውሻ ይውለድ ልበል”ና ከ‹አየር› ልውጣ፡፡ ቻው!
ነገር የሚፈልገኝ ሰው ይኖር ይሆን እንዴ? – ma74085@gmail.com
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment