Yakob's Point of Views and News, Ethiopian politics and News, Cultures, Musics etc

Saturday, March 23, 2013

እንጩህ፡፡ መንግስት ሰምቶ አቤት እንዲለን ሳይሆን ህዝብ ሰምቶ እንደኛ እንዲጮህ እንጩህ!!

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሂደት ውስጥ መንግስት በተቃዋሚ ኃይሎችና በጋዜጠኞች ላይ በተከታታይ የወሰዳቸው አሸማቃቂ እርምጃዎች የተለያዩ ውጤቶች አስከትለዋል፡፡ ከነዚህ ውጤቶች መካከል ዝምታ በጣም አስከፊው ነው፡፡ ዝምታውን በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡
አንደኛው የብዙሃኑ ዝምታ ነው፡፡ የዚህ ዝምታ ምንጭ በአመዛኙ ከፍርሃት የመነጨ ይመስለኛል፡፡ በስርዓቱ ላይ ያለውን ተቃውሞ ለመግለፅ የፍርሃቱን ምህረት የለሽ ቅጣት በመፍራት በአገሪቱ ላይ የሚፈፀሙ ግፎችን በዝምታ ይመለከታል፡፡
ሁለተኛው ዝምታ የተቃዋሚው፣ የምሁራንና የጋዜጠኞች ዝምታ ነው፡፡ የዚህ ዝምታ ምክንያት ደግሞ ተስፋ መቁረጥ ይመስለኛል፡፡ የስርዓቱን እርምጃዎች በመተቸትና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እይታቸውን በማካፈል የሚታወቁት አብዛኞቹ ሰዎች በስርዓቱ ላይ ተስፋ በመቁረጣቸው የመንግስትን እርምጃዎች መተቸትን ተራራ እንደማጠብ ቆጥረውታል፡፡ በዚህ መካከል ግን የልማታዊ መንግስት ስርዓት እየወፈረና እየፋፋ መሄዱን ቀጥሏል፡፡

በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሃሳብን መግለፅና በድንቁርና መሰረት ላይ የቆመውን የልማታዊ መንግስት ስርዓት መፈተን እየተቻለ ዝምታን አማራጭ ማድረግ ቢያንስ ሁለት መሰረታዊ ጉዳቶች ያስከትላል፡፡

አንደኛው፣ ዜጎች በመንግስት እርምጃዎች ሁሉ እየተስማሙ ወይም ሳይከነክናቸው እንዲቀጥሉ ያደርጋል፡፡ ይህም የሚሆነው በአማራጭ ሃሳቦች እጦት ነው፡፡ ትንሽ አማራጭ ሃሳቦች ማግኘት ያልቻለ ህዝብ የመንግስትን ሃሳብ እየተቸገረም ቢሆን ይውጣል አለበለዚያም ከአገራዊ ጉዳዮች ራሱን አግልሎ በሌሎች እንቶ ፈንቶ ወሬዎች ይጠመዳል፡፡ ይህ ደግሞ ልማታዊ ስርዓቱን በማይናወጥ መሰረት ላይ ያቆመዋል፡፡ ለወደፊቱም ለዲሞክራሲ የማይመች ማህበረሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
ሁለተኛው የዝምታው ጉዳት መንግስት ከአሁን በፊት እየተግደረደረም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚቀበላቸው የተቃውሞ ሃሳቦች ምንጫቸው እንዲደርቅ ማድረጉ ነው፡፡ በዚህም የመንግስትን እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ የ’እንደልቡ’ እርምጃዎች ያደርጋቸዋል፡፡ ተቃውሞን ፈርቶ የሚያለሳልሰው እርምጃ ወይም አቋም ሊኖር አይችልም፡፡ ይህም የስርዓቱን ጉልበት በመጨመር መከራችንን ያበዛዋል፡፡

ስለዚህም ከዝምታ ዋሻችን ወጥተን የሚሰማንን በመግለፅ ኮርማውን ከውፍረት እንታደገው፡፡ ፌስቡክንና ትዊተርን የመሳሰሉ የማህበረሰብ ድሮችን ጨምሮ ሌሎች የተገኙ መንገዶችን በመጠቀም ሃሳባችንን እንግለፅ፡፡ ልማታዊ መንግስቱን መታገል የሚቻለው የሃሳብ ሚሳኤል በማስወንጨፍ ነው፡፡ ከሃሳብ በላይ የሚያፈርሰው ኃይል ሊኖረው አይችልም፡፡ ጠብመንጃን ከመከላከል በላይ ሃሳብ እንዳይገለፅ ለመከላከል ተግቶ የሚሰራውም ለዚህ ነው፡፡ ዝምታችን የስርዓቱ ዋስትና ነው፡፡
መልዕክቴ ይህ ነው- እንጩህ፡፡ መንግስት ሰምቶ አቤት እንዲለን ሳይሆን ህዝብ ሰምቶ እንደኛ እንዲጮህ እንጩህ፡፡ ስርዓቱን በጩኸት እናፍርሰው፡፡ 
http://walelgnemekonnen.wordpress.com/2013/03/22/lets-mobilize-the-people-by-shouting/

No comments:

Post a Comment