ከአቤ ቶኪቻው
ተዓምረኛው ኢቲቪ ለማርች ስምንት የሴቶች ቀን መታሰቢያ አንድ ዶክመንተሪ ፊልም አሳይቶናል። ፊልሙ የዛሬ አመት ተላልፎ እኛም የአቅማችንን አስተያየት ሰጥተንበት ነበር። ታድያ ዛሬም ኢቲቪዬ ፊልሙን ደግሞ አሳይቶናል። ታድያ መድገም ብርቅ ነው እንዴ… እኛም አስተያየታችንን እንድገመዋ!
በመጀመሪያ አበሻ እንደመሆኔ መጠን ጭቆናን “እምቢ” ብለው ፋኖን ለዘመሩ ታጋዮች ትልቅ አክብሮት እንዳለኝ ያለ ሽሙጥ እገልፃለሁ።
ተስፋዬ ገብረ አብ ከተረካቸው ትረካዎች በሙሉ “የቁንድዶ ፈረስ” ትረካ በጣም የመሰጠችኝ ናት። እስቲ ለማስታወስ ልሞክር…
ሐረር አካባቢ፤ የጋሪ ፈረሶች የሚደርስባቸው የስራ ጫና እጅግ በጣም ከባድ ነበር። ከስራ ጫናው እኩል ደግሞ ዱላም አለው። ልክ አሁን አሁን ደሞዛችን አነሰ ብለን “ኡኡ” ስንል “ለአባይ እና ለሌሎች ልማቶች ደግሞ መዋጮ አዋጡ” ተብለን መከራችንን እንደምናየው ማለት ነው። በዚህ ላይ እነዚህ የጋሪ ፈረሶች ስራውና ዱላ የሚደራረብባቸው አንሶ ጌታቸው (አባ ፈርዳው) ቀለባቸውንም በአግባቡ አይሰፍርላቸውም ነበርና ከሰውነት ጎዳና ወጥተው ክስት ጉስቁል አሉ።
ይሄን ግዜ “እምቢኝ” አሉና “ቁንድዶ” ወደተባለ ጫካ ገቡ። ከዛም ባህሪያቸው ተለውጦ እንደፈረስ ሳይሆን እንደ እንደ አውሬ ሆኑ። ማን ወንድ መጥቶ ዳግም ወደዛ የጋሪ ባርነት ይመልሳቸው? ማንም።
ታድያ ፈረሶቹ እዛው ጫካ ውስጥ መሽገው እንዳሻቸው እየበሉ እንዳሻቸው እየቦረቁ አማረባቸው። ወዘናቸውም “ጢም” አለ።
“በአሁኑ ግዜ የሀረር አካባቢ ነዋሪዎች የኦህዴድ አባላትን እስከ መቼ የጋሪ ፈረስ ትሆናላችሁ? አንዳንዴ እንኳን የቁንድዶ ፈረስ ሁኑ እንጂ…! እያሉ ያሽሟጥጧቸዋል።” ብሎናል ተስፋዬ። (ልክ ነኝ አይደል ተስፋዬ…? “ይሄንን እኔ አላልኩም” ካልክ እኔ ለማለት እገደዳለሁ…!(ፈገግታ))
እናም እኔ በበኩሌ የቁንድዶ ፈረስነትን አደንቃለሁ። አላማው ልክ ነው አይደለም የሚለው ጥያቄ በይደር ይቆይ። ነገር ግን በደል ሲበዛ “እምቢ” ማለት ከአባት የወረስነው ነው። ዛሬ የሽብረተኝነት አዋጅ ወጥቶ ሳይከለከል አይቀርም እንጂ አንድ ዘፈን ትዝ ይለኛል…
“ደብቆታል መሰል ሶማ በረሃው
“እምቢ” ያለው ጎበዝ የታል ሽፈራው” የሚል ዘፈን።
በአሁኑ ወቅት፤ ይህንን ዘፈን በይፋ መዝፈን የሚቻል አይመስለኝም። ምክንያቱም በሽብርተኝነት አዋጁ አንድ ግለሰብ፤ በዘፈን በፅሁፍ እና በተለያዩ መንገዶች “ሽብርተኛን” እንኳንስ ሲያበረታታ ተገኝቶ ይቅርና፤ “አበረታቷል” ተብሎ ሲታሰብም “ጉዱ ይፈላል” ይላል። በተጨባጭ እንደምናየው ደግሞ እንኳንስ እምቢ ብለው ሶማ ጫካ ገብተው ይቅርና በከተማው ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች ራሳቸው “አሸባሪ” ስለመሆናቸው መረጃው አለ። ማስረጃው ጠፍቶ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩም እኛም የጨነቀን…! ስለዚህ “ደብቆታል መሰል ሶማ በረሃው እምቢ ያለው ጎበዝ የታል ሽፈራው…” ብሎ ማዜም አይቻልም ማለት ነው።
ለማንኛውም፤ ዘፈኑ ግን “እምቢ” ባይነትን እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙሃን የሀገሬ ሰው እንደሚያደንቅ ያስረዳልኛል። አዎ አንዳንዴም እምቢ ማለት ጥሩ ነው። “እምቢ… እምቢ ለሀገሬ! እምቢ… እምቢ ለክብሪ! እምቢ… ታታታታ” ፉከራው ራሱ ማማሩ።
ስለዚህ ቐሽ ገብሩ፤ አሞራውና ሌሎችም “እምቢ” ባይ ታጋዮች “እምቢ” በማለታቸው አደንቃቸዋለሁ። እንኳንም እምቢ አላችሁ!
ወደ ቐሽ ገብሩ ስንመጣ የዶክመንተሪው አዘጋጆች ልብ ያላሉት ወይም ደግሞ “ምን ታመጣላችሁ” ብለው ችላ ያሉት አንድ ስህተት የፌስ ቡክ ወዳጆቼ አግኝተው ነበር። ልብ በሉልኝ ህውሃት ሆዬ ቐሽ ገብሩን መትረየስ ሲያሸክማት ገና የአስራ ሶስት አመት ልጅ ነበረች። ከፈለጋችሁ አስሉት በአስራ ዘጠኝ ስድሳ አንድ ተወለደች። በአስራ ዘጠኝ ሰባ አራት ወደ ትግል ገባች። ማነው ሂሳብ የሚችል…? በሉ እስቲ አስሉልኝ። ሰባ አራት ሲቀነስ ስድሳ አንድ እኩል ይሆናል፤ አስራ ሶስት። ዘጋቢው ፊልም ሲቀጥልም “…ትግሉን በተቀላቀለች በጥቂት ወራት ውስጥ እጇን ተመታች። እንደዛም ሆና መትረየስ ትሸከም ነበር።” ይላል። ጉድ በል ህውሃት…! አይሉኝም?
በዛ ሰሞን አለም ሲነጋገርበት ከሰነበተባቸው ነገሮች ውስጥ በኡጋንዳ የሚገኘው የሎርድ ሬዚስታንት አርሚ መሪ፤ ጆሴፍ ኮኒ ህፃናትን ጦርነት ውስጥ እየማገደ ነው በሚል ታድኖ ይከሰስ ዘንድ የተጀመረው “ኮኒ ሁለት ሺህ አስራ ሁለት” የሚል እንቅስቃሴ ነው። በአለም አቀፍ ህግ፣ አረ በኢትዮጵያ ህገ መንግስትም ቢሆን ህፃናትን ለጦርነት ማሳተፍ የለየለት ወንጀል ነው። በእግዜሩ ዘንድም ያስጠይቃል።
እና ህውሃት የአስራ ሶስት አመቷን ህፃን ሙሉ “ቐሽ ገብሩ” ን በጦርነት ማሳተፉ ሳያንስ የግፉ ግፍ ደግሞ ለማርች ስምንት የሴቶች መብት ክብረ በዓል ላይ ታሪኳን እንደ ጥሩ ነገር ዘገበልን። እውነቱን ለመናገር ይሄ ትልቅ የወንጀል መረጃ ነው። እንደኔ እምነት ይህንን መረጃ ያጠናከሩ ሰዎች የውስጥ አርበኝነት ስራ እየሰሩ ነው። ይሄ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ገና በርካታ መረጃዎችን ያወጣል። እዝችው ላይ ሙሉ ወይም ቐሽ ገብሩ ገና አስራ ስምንት አመት እንኳ ሳይሞላት አንድ ጎረምሳ በፍቅር ስም አስረግዞ እስከማስወረድ እንድትደርስ እንዳደረጋትም ዶክመንተሪው ይዘግባል። ሰውየው ከሷ ጋር ያሳለፈውን ፍቅርም ሲናገርም በኩራት ነው። እንዴት ነው ነገሩ… እኛ መሀሙድ አህመድ በአንድ ዘፈኑ ላይ “ሸግየዋ ጉብሊቷ… የአስራ አምስት አመቷ እንዴት ነሽ በሉልኝ የምታውቁ ቤቷን” ብሎ ስለዘፈነ አይደል እንዴ ከህፃናት መብት አንፃር ወንጀል ነውና ይቅርታ መጠየቅ አለበት እያልን የምንሟገተው? እንዲህ የባሰውን ነውር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አየነው። ለዚህ ነው አይናችን የተርገበገው…?
ወዳጄ እንዴት ሰነበቱ አይገርምዎትም ይሄ ሁሉ መንደርርደሪያ መሆኑ… ይበሉ ወደ ዋናው ጉዳይ ተያይዘን እናምራ
እናልዎ… ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተለያየ ግዜ የተለያየ ዘጋቢም አወዛጋቢም ፊልሞችን ያቀርብልናል።
በዛ ሳምትን ያየነውም የቐሽ ገብሩ ዶክመንተሪም የዚሁ አካል ነው። እንግዲህ ከላይ ያነሳነውን በቐሽ ገብሩ የተጋለጠውን ህፃናትን ወደ ጦርነት የማሰማራት እና ለአቅመ ህይዋን ያልደረሱ ሴቶችን የማማገጥ ወንጀል እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለሚከታተሉ አካሎች እንተወው እና የፈረደባትን ይቺን ህፃን “እምቢ” እንዳለች ጀግና እንቁጠራት። ቆጠርናት…!
ኢህአዴግ ደርግን ብዙ ግዜ ደርግ በጦርነት የማረካቸውን ታጋዮቼን የማያምኑበትን እንዲናገሩ ያሰቃያቸው ነበር፤ ከዛም እምቢ ሲሉት ያስራቸዋል፤ ይገድላቸዋል። ብሎ ይወቅሳል። ይቀጥልናም ቢሆንም ግን፤ “እንደ አሞራው ሁኑ እንደ ቐሽ ገብሩ ሁኑ ብሎ ይመክረናል። እኛም ምክር የምንሰማ ልባሞች ነንና እሺ ብለን እንደ አሞራው፤ እንደ ቐሽ ገብሩም ለመሆን እንታትራለን ከዛ ውጤቱ ምን ይሆናል አይሉኝም…? ለምን እጠይቅሀለው እያወቅሁት…? አሉኝ እንዴ!?
ሰሞኑን አቶ አንዷለም አራጌ ላይ የሆነውን ነገር ሰምተዋል። አንዷለም አራጌ እንደ አሞራው ሁኑ ከመባሉ በፊትም እንደ አሞራው “እምቢ” ባይ ነበር። ለዛውም ጫካ ሳይገባ ፊት ለፊት እምቢ ብሎ የተጋፈጠ ደፋር የተቃማዊ ፓርቲ አመራር ነው። ምን ዋጋ አለው አንዷለም እንደ አሞራው “እምቢ” ቢልም ኢህአዴግ ደግሞ እንደ ደርግ “እምቢ” ማለት አይቻልም ብሎ አሰረው። ማሰር ብቻ ቢሆን በስንት ጣዕሙ ጎረምሳ አስገብቶ አስደበደበው እንጂ!
ማርች ስምንት የአለም ሴቶች ቀን ነው። በአለም ላይ ያሉ ሴቶች ቀደም ሲል ሲደርስባቸው የነበረ ጭቆና ይብቃ የተባለበት ቀን። ይህ ቀን፤ የህውሃት ሴቶች ቀንም የአንድነት ሴቶች ቀንም፤ የጋዜጠኛ ሴቶች ቀንም፣ የሁሉም ሴቶች ቀን ነው።
ርዕዮት አለሙ አሳሪዎቿ የጠላነውን አብረሽን ከጠላሽ ትለቀቂያለሽ ብለዋት ነበር። ቃል በቃል ሲነገር “ኤልያስ ክፍሌ የተባለው ጋዜጠኛን አሸባሪ ነው መሰስክሪበት እና ትለቀቂያለሽ” ተባለች። እርሷም እኔ “በወንጀለኝነት አላውቀውም” ብላ ድርቅ አለች። እንግዲያስ ብሎ ኢህአዴግም አስራ አራት አመት ፈረደባት። ቐሽ ገብሩን ደርግ የያዛት ግዜ “የህውሃት ሰዎችን ወንጀለኛ ናቸው ብለሽ መስክሪባቸው” አላት እምቢኝ ብላ ድርቅ አለች ሞት ፈረደባት። እንግዲህ ቐሽ ገብሩ እና ርዮት አለሙ አንድ ናቸው “እምቢኝ” ብለዋልና። ደርግ እና ኢህአዴግስ…? የመጣው ይምጣ ደፍሬ ልናገር ነው..! አዎ ደርግ እና ኢህአዴግም አንድ ናቸው። እምቢ ያላቸው ላይ ሁሉ ይፈርዳሉና። በነገራችን ላይ የደርግ ፕሮፖጋንዳ ሰራተኞች ቐሽ ገብሩን ለማናገር መከራቸውን ሲያዩ የነበረውን ያህል የኢህአዴግ ጋዜጠኞችም በተደበቀ ካሜራ ሳይቀር ርዮትን ለማናገር አበሳቸውን ሲያዩ ነበር። ነገር ግን ቐሽ ገብሩም ርዮትም አለሙም ፍንክች የአባ ቢላው ልጅ ብለዋል። ወይ መገጣጠም…! አይሉልኝም?
እና ታድያ የሴቶች ቀን ክብረ በዓል ሲዘከር መንግስት ርዕዮትን አስሮ ስለ ቐሽ ገብሩ ሲተርክ የአራዳ ልጆች ሰሙ። ሰምተውም ጠየቁ “ሼም የለም እንዴ በአገሩ!?” አሉ ዝርዝር ያለው የስራ ሂደት ካለ መልስ ያምጣ…!
በጥቅሉ መንግስት እነ ርዕዮትን፣ እነ እስክንድርን፣ እነ ውብሸትን፣ እነ ሂሩትን፣ እነ አንዷለምን እነ ናትናኤልን፤ ስንቱን ጠርቼ እዘልቀዋለሁ? በጅምላው እምቢ ያሉትን ሁሉ እያሰረ እና እየገረፈ “ደርግ ታጋዮቼን አሰረ፣ ገረፈ፣ ገደለ” ብሎ ዋይ ዋይ ማለት ውሃ የማያነሳ ወቀሳ ነው። መፅሐፉም ይላል “የሌሎችን ጉድፍ ከማየትህ በፊት በአንተ አይን ውስጥ ያለውን ቆሻሻ ተመልከት…”
በመጨረሻም ያወጋነውን ለፍሬ ይበልልን
አማን ያሰንብተን! https://abetokichaw.wordpress.com/
No comments:
Post a Comment