ስድስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ለማስመረጥ የተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ ከምርጫው ሂደት ጋርና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ምርጫው ተከናውኖ፣ በዚሁ ዕለት ምሽት 12 ሰዓት ላይ፤ ውጤቱ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡
መራጮች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከጥንታውያን ገዳማትና አድባራት፤ ከካህናት፤ ከምእመናን፤ ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት የተወከሉ ሲሆኑ ጠቅላላ ቁጥራቸው 800 መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው፡- በመጨረሻ እጩ ሆነው የሚቀርቡ አምስት እጩ ፓትርያርኮች የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ አመልክቷል፡፡ የምርጫውን ሂደት ለማስፈጸም የወጣው መግለጫ “ምእመናን ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው ማንነታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በመያዝ ለእጩነት የሚያስቡትን አባት አስመራጭ ኮሚቴው ጽ/ቤት ድረስ በአካል በመቅረብ እንዲሁም ከሀገር ውጪ የሚገኙ በፋክስ ቁጥር 0111567711 እና 0111580540 ከየካቲት 1 እስከ 8 ቀን 2005 ዓ.ም እንዲጠቁሙ” ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ስድስተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በመሆን የሚመረጡት አባት እሑድ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በዓለ ሢመቱ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም መግለጫው አመልክቷል፡፡
ከየሀገረ ስብከቱ በመራጭነት የተወከሉ ሰዎች የካቲት 19 ቀን 2005 ዓ.ም አዲስ አበባ እንዲገቡ ያዘዘው የአስመራጭ ኮሚቴው መግለጫ እግዚአብሔር አምላካችን የወደደውንና የፈቀደውን በመንበሩ ያስቀምጥ ዘንድ ካህናትና ምእመናን ከየካቲት 1 እስከ 8 ቀን ድረስ አምላካቸውን በጸሎት እንዲጠይቁ ለአንድ ሱባኤ የሚቆይ የጸሎት ጊዜ መታወጁን አስታውቋል፡፡
eotc-mkidusan.org
posted by Aseged Tamene
ምንጭ እና የተወሰደበት ማታቅሻ http://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/02/07/434525/
No comments:
Post a Comment