የዛሬ አስር አመት በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል ለሁለት ዓመት ያክል በተደረገ አላስፈላጊ ጦርነት ቁጥሩ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ የሆነ የሰው ህይወት በከንቱ ከሁለቱም ወገን ተሰውቶበታል ። በመሰረቱ ዛሬ ኤርትራ ተብላ የምትጠራው አገር ወያኔ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት የኢትዮጵያ አካል እንደነበረች ይታወቃል ። ወያኔም በተመሳሳይ የመገንጠል አላማ ስላለው ላደረገው የጥፋት ተግባሩ ኮራበት እንጂ አላዘነም ፤ አላፈረም ።
የወያኔ የግንጠላ ምኞት እስከ ዛሬ ድረስ ያልተፈጸመበት ምክንያት አለው ፤ ወያኔ ወደ ስልጥን ሲመጣ በጊዜው ምንም ተቀናቃኝ ባለመኖሩ ትግራይን በባዶ እጅ ይዞ መሄዱ ትርፉ ውድቀትና ድህነት መሆኑን በመረዳቱ ተቀናቃኝ ኃይል እስከሌለ ለምን ጠቅላላ ኢትዮጵያን አልይዝምና አልበዘብዝም በሚል እኩይ እምነት ተነስቶ እንደሆነ ይታወቃል ።
ስልጣኑንም በሥመ ኢትዮጵያዊነት ይዞ በመቆየት በብዝበዝና በዝርፊያ የሚገኘውን ሀብት ለትግራይ ግንባታ ሊሰጥ የሚችለውን አሌ የማይባል ጥቅም በመመልከት ፤ በስልጣኑም ለመቆየት የሚያሰጋው አንዳችም ኃይል አለመኖሩን በማስተዋሉ ይሄው እስከ ዛሬ ያለ ስጋት የያዘውን ይዞ ምዝበራውን በሰፊው ተያይዞት ቆየ እንጂ የተነሳበትን የደደቢት አላማውን ስቷል ማለት አይደለም ። ስለሆነም ያለ ሕዝብ ፈቃድ ኤርትራን ከእናት አገሯ ነጥሎ እንድትገነጠልና ኢትዮጵያም ያለ ባህር በር እንድትቀር እንዳደረገ ሁሉ ፤ የሱንም ያደባባይ ሚስጥር የሆነ ምኞት ማንም ስለፈቀደ ወይም ስላልፈቀደ ሳይሆን ልክ የሻቢያን መገንጠል አለ ሕዝብ ፈቃድ እውን እንዲሆን እንዳደረገ ሁሉ የሱንም የግንጠላ ምኞት በተመሳሳይ ሁኔታ እንደ ወዳጁ ሻቢያ ትግራይን ከናት አገሯ ገንጥሎ ለመሄድ አመቺ ጊዜን እየጠበቀ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው ።
ዛሬ ትግራይ ከማናቸውም የኢትዮጵያ ጠ/ግዛቶች በበለጠና በተለየ የስስት አይን ስለምትታይ መፈክሩ “ ሁሉም ነገር ወደ ትግራይ” ሆኗል ። በትግራይ የሚሰሩት የአየር ማረፊያዎች ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ፤ የመገናኛ መንገዶች ፤ የውሃ ግድቦች ፤ ከመሃል አገር እየተነቀሉ ወደ ትግራይ የተጓዙት የጨርቃ ጨርቅ ፤ የሲሚንቶ፤ የመድሃኒት ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ግንባታዎች ፤ የአውቶሞቢል መገጣጠሚያዎች ፤ ከብዙ በጥቂቱ ለአብነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ ፤ በአንፃሩ ለተቀሩት ጠ/ግዛቶች የሚደረግ ግንባታ አይታይም ፤ ካለም ከትግራይ ልማት ጋር ሲነፃፀር እጅግ በጣም ያነሰ በመሆኑ ልማት ተደርጓል ለማለት አያስደፍርም ። ትግራይን እንደ ወለዱት ልጅ ሲንከባከቡ የተቀረውን ግን በገዛ ሀብቱ እየተንደላቀቁና እየተጠቀሙ እንደ እንጀራ ልጅ ማየታቸው አሳዛኝ ትርኢት ሆኖ አግኝቼዋለሁ ።
በእርግጥ አሁን ያለው አገዛዝ ለግንጠላው መሰናዶ የተቀረውን የኢትዮጵያ ክፍል አለ ሃፍረት እንደ ጥገት ማለቡን እንደቀጠለ ይገኛል ፤ በአንዲት ትልቅ አገር አንጡራ ሀብት ያለ ከልካይ እየተዘረፈ አንዲት ትንሽ ጠ/ግዛት መገንባቱ ፤ አንድን ክፍል እያስተማሩ ሌላውን በድንቁርና ማስቀመጡ ፤ አንዱን እያበሉ ሌላውን ማስራቡና ያልተመጣጠነ አድሎአዊ የሆነ አሰራር የሚካሄደው አገሬ ብሎ ተቆርቁሮ ተደራጅቶ የተነሳ ተቃዋሚ እንደሌለ በማወቃቸው ፤ ጊዜና ሁኔታዎችም ስለተመቻቹላቸው ጭምር እንደሆነ ይታወቃል ፤ ይህንንም አጋጣሚ በመጠቀም ህልማቸውን እውን ለማድረግ እንደ መዥገር ተጣብቀው መመጥመጡን በሰፊው ተያይዘውት እናያለን ።
እንደዚህ ያለ ወርቃማ አጋጣሚ በሚሊዮን ዓመት አንድ ጊዜ እንኳን የማይከሰተውን በነሱ ጫማ ሆኖ ለሚመለከት አጥፊ ህሊና ላለው እንዴት የሚያጓጓና የሚያስመረቅን ሊሆን እንደሚችል በገመትም አያዳግትም ።
እንግዲህ ወያኔዎች ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ጀምሮ ምኞታቸው ኤርትራን ከማስገንጠል ባሻገር እነሱም ትግራይን ገንጥሎ ለመሄድ ስለሆነ ፤ እኛ ታላቋ ኢትዮጵያ ፤ አንድ ኢትዮጵያ እያልን ስለምናለቅስላት አገር ፍቅርም ፤ ደንታም እንደማይኖራቸው ማወቅና መረዳት የግድ ይላል ።
ባጋጣሚ ኢትዮጵያ አገራችን ዛሬ ጠባቂና ዘበኛ ባጣችበት ወቅት ስለመጡ ሀብት ንብረቷን ፤ ቅሪቷን ፤ ዘርፎ አገሪቷን በጎሳ ፤ በሃይማኖትና በመሳሰሉት ከፋፍሎ በለስ ቀንቷቸው እነሱ ወደሚሄዱበት በሚሄዱበት ወቅት ላላማቸው መሳካት የተቀረው ኢትዮጵያዊ እንቅፋት እንዳይሆንባቸው ፤ ማለትም የሚያስገነጥሉትን የትግራይ ጠ/ግዛት አለ አንዳች ስጋት መገንባትና ማጠናከር ያስችላቸው ዘንድ ቀደም ብለው ስልጣኑ ላይ እንደተፈናጠጡ ሲሰሩበት የቆዩበት የረጅም ጊዜ ውጥን እንደሆነ ይታወቃል ። ይህንን ዓላማቸውን እንኳን የማስተዋያ አይምሮ ያለው የሰው ልጅ ቀርቶ ፤ ሳር የሚግጡት እንሰሳትም በውል የሚያውቁት ተግባር ነው ብል ነገሩን ማጋነን አይመስለኝም ።
ወያኔዎች ዛሬ ኢትዮጵያዊው የደከመ ኃይል መሆኑን በመረዳታቸው ከጎንደርና ከወሎ ሰፊና ለም የሆኑ ቦታዎችን ቆርሰው ወደ ትግራይ ጠ/ግዛት ቀላቅለዋል ። ከነዚህም ከጎንደርና ከወሎ የተወሰዱ ቦታዎች ላይ ነዋሪ የነበሩትን ዜጎቻችንን በማፈናቀል ፤ ሴቶችና ልጃገረዶችም ከትግራይ ወንዶች በግድ እንዲወልዱ በማስገደድ ፤ በመድፈር ፤ የአካባቢውን ነዋሪ ሕዝብ በትግሪኛ ተናጋሪው ለመተካት የተደረገው የቅኝ ገዢዎችን መርሆ የተመረኮዘ ፋሽስታዊ አሰራር ስንመለከት ለግንጠላውና ድብቅ ላልሆነው አላማቸው ምን ያክል ጠንክረው እየሰሩ እንደሆነ ይመሰክራል ።
እነዚህ የጥፋት መልዕክተኞች ለኢትዮጵያ ካላቸው ጥላቻ በመነሳት ፤ ለወደፊትም ሕዝብ ከተባበረ ለምኞታቸው እንቅፋት እንደሚሆንባቸው አስቀድመው ስላወቁ ከፈጠሩት የጎሳና የሀይማኖት ቅራኔ ባሻገር ፤ የጎረቤት አገርም እነሱ በሚሄዱበት ወቅት በቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ቂም በቀል ይዞ በሕዝባችን ላይ እንዲነሳ ፤ በአረጋችን ላይ መረጋጋት እንዳይኖር ለማድረግ ፤ ዛሬ ሱማሊያ ውስጥ በኢትዮጵያ ሥም በመግባት የሚያደርሱት ኢሰብአዊ ጭፍጨፋ ነገ ሱማሌ እራሷን ስትችል ይህንን ቂም በማዘል በሐገራችን ላይ የሚኖራት አመለካከትና በሐገራችንም ሰላም እንዳይኖር ልታደርግ የምትችለውን ጥፋት ከወዲሁ ለመስራት ታቅዶ የታወጀ ጦርነት እንደሆነ ማወቁ ተገቢ ነው ።
ይህ ለወደፊት ግንጠላውን እውን አረጋለሁ ለሚለው ወያኔ የጊዜ መግዣና የመጠናከሪያ ስልት መሆኑ ታምኖበት በጥናትና በዘዴ የተፈጸመ ወረራ መሆኑን ለመረዳት ነብይነትን አይጠይቅም ። ወያኔዎች በዚህ ተንኮል ብቻ አላበቁም : ባራቱም ማዕዘን ለኢትዮጵያ ጠላት መሸመቱን በሰፊው ተያይዘውታል ፤ በምዕራብ ኢትዮጵያ ከጎንደር እስከ ጋምቤላ ድረስ እርዝመቱ 1600 ኪ/ሜትር የሆነና ጥልቀቱ ደግሞ ከ 30 እስከ 50 ኪ/ሜትር የሚደርስ ለምና በተፈጥሮ ማዕድናት የዳበረ መሬታችንን በማናለብኝነት ለሱዳን መንግሥት አሳልፎ ሰጥቷል ። የሱዳን መንግሥትም ለተደረገለት መልካም ስጦታ አጸፋውን ለመመለስ ለወደፊት በወያኔ ሂሳብ ትግራይ እራሷን ከኢትዮጵያ ገንጥላ እንደ አንድ አገር ትቆማለች ብሎ ለሚያስባት እንደ ዋና የንግድ በር ሆኖ የሚያገለግል ከፖርት ሱዳን ተነስቶ አዲግራት የሚደርስ የባቡር ሀዲድና በተጨማሪም ሱዳንና ትግራይን የሚያገናኝ ትልቅ የአውራ መንገድ ለመዘርጋት የሱዳን መንግሥት ቃል እንደገባላቸው ተዘግቧል ።
ይህን ሁሉ ወንጀል በአገራችን ላይ የፈጸመው ወያኔ እስካሁን የሰራው ጥፋት ሁሉ አላረካ ብሎት ፤ ዛሬ የሐገራችን አርሶ አደር ገበሬ እራሱንና ቤተሰቡን ከመመገብ አልፎ ለህብረተሰቡ ይተርፍ የነበረውን ፤ በማዳበሪያ እዳና በጥላቻ ፖለቲካ የተነሳ ገበሬው በየምክንያቱ አርሶ መብላት እንዳይችል አድርጎት ለረሃብ እንደዳረገው እያየን ነው ።
በሌላው ወገን ደግሞ ይህ ገበሬ እንዳያርሰው የተደረገውን መሬት ለጅቡቲና ለሳውዲ አረቢያ መንግሥታት አልምተው ሕዝባቸውን መመገብ ይችሉ ዘንድ በማለት ከሐገራችን ገበሬ ቀምቶ ለባዕዳን መንግሥታት በብዙ ሺህ ሄክታር የሚቆጠር ለም ቦታዎችን እየቸበቸበው ይገኛል ። “የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች” ይሏል ይሄ ነው ።
እንግዲህ ኢትዮጵያ በመሃል አገር በጎሳና በሃይማኖት ልዩነት እንዲጨራረስ ሆን ተብሎ በገዢው ክፍል እየተቆሰቆሰና እየተበረታታ ባለበት ሁኔታ ፤ በሌላው ወገን ከጎረቤት አገሮች ጋር በሰላም መኖር እንዳይቻል በምስራቁም በምዕራቡም የጠላት አይነት እየመለመለልን ባለበት ወቅት ፤ ዛሬ ደግሞ ከኤርትራ ጋር የጦር ፍልሚያ ለማድረግ ደፋ ቀና ማለት አላማው ለምን ይሆን?
በእውነት ኢትዮጵያዊነት የማይሰማቸው ወያኔዎች ዛሬም ለባድሜና ለዛላምበሳ በምናደርገው ጦርነት ኑና ሙቱልን ብለው የኢትዮጵያን ሕዝብ በድፍረት ይጥሩት? “ያሁኑ ይባስ” ይላል ያገሬ ሰው ነገር አልጥም ሲለው ፤ የሚሉን እኮ “ከባልሽ ባሌ ይበልጣልና ሽሮ አበድሪኝ” ነው ጎበዝ? እጅግ ተንቀናል የሚሉን ከገባን ። እውነት ሻቢያና ወያኔ እኛ እንድንቀበላቸው እንደሚፈልጉት በጠላትነት አይን የሚተያዩ ናቸው ? ወይስ ለኛ ግልጽ ያልሆነልን ድራማ እየሰሩብን ነው? የኢትዮጵያ የሆነው ለም መሬት ተቆርሶ ለሱዳን ሲሸጥ ፤ ለሳውዲ አረቢያና ለጅቡቲ ሲለገስ ፤ ታዲያ ለኤርትራስ ለምን እንደ ሌሎቹ ድርሻዋ አይሰጣትም?
ወያኔዎቹ የሚሉን የመሬት ስጦታው ከኢትዮጵያ ተቆርሶ እንጂ ከትግራይማ እንዴትስ ተሞክሮ ! መታሰቡስ ! ነው የሚሉን ? “ኢትዮጵያ የጋራችን ትግራይ የግላችን” አይገርምም ? ይሄ አድራጎታቸው እራሱ ወያኔዎች ኢትዮጵያን እንደ አንድ የባዕድ አገር የሚመለከቱና ስለ ኢትዮጵያ ግድ እንደሌላቸው መሆናቸውን ነው ። አገራችን የሚሉት ትግሬን እንጂ ኢትዮጵያን እንዳልሆነ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መስታወት ነው ። የሻቢያ የመሬት ጥያቄው ከትግራይ ጠ/ግዛት ባይሆንና ጥያቄው ከባሌ ወይም ከጅማ መሬት ማግኘት ቢሆን ኖሮ ልክ እንደ ጅቡቲና ሳውዲ አረቢያ መንግሥታት አይንህ እስካየ ፈረስህ እስከጋለበ ያንተው ነው ተብሎ ተመርቆ ይሰጠው እንደነበረ ለማንም የተሰወረ አይደለም ። ችግሩን የፈጠረው ከትግራይ መሬት የመጠየቁ ጉዳይ ነው ። ታዲያ ዛሬ በምዕራቡ ኢትዮጵያ ያለው ሕዝባችን አገሬንና ዳር ድንበሬን አላስነካም ፤ አላስደፍርም ፤ ብሎ ከድርቡሽ ጦር ጋር በሚዋደቅበት ባሁኑ ጊዜ ፤ ከፊቱ የድርቡሽ ጦር ከኋላው የወያኔ ጦር መሃል አስገብተው እየቆሉት ባናቱ ላይ እንደ ገና ዳቦ ከላይና ከታች እሳት ሲያነዱበት እንዴትና በምን ሂሳብ ቢታሰብ ነው ታዲያ ዛሬ ለባድሜና ለዛላምበሳ ሕዝባችን መስዋዕት እንዲከፍል የሚጠየቀው?
እንግዲህ ይህ በኢትዮጵያ ሥም የተቋቋመው የጦር ሠራዊት ባንድ ወገን ዳር ድንበሬን አላስደፍርም በማለት የሠራዊቱ ተግባር የነበረውን ሥራ እየሰራ ያለውን ዜጋችንን ከድርቡሹች ጋር አብሮ እየወጋ ፤ በሌላ በኩል ባድሜን ከወራሪ ለመጠበቅ ጥሪ አለብኝና ተባበሩኝ ብሎ ለሕዝብ ጥሪ ማቅረብ ኢትዮጵያዊውን ከመናቅ የመጣ ነው? ወይንስ ለቀልድ የተሰነዘረ ማላገጥ?
በወያኔ ጭንቅላት ስሌት ሳይሆን በንጹህ ኢትዮጵያዊ አይምሮ ቢታሰብ በአንድ ወገን አገር ቆርሰው ያውም ለሙን መሬት እየሰጡ ፤ በሌላ ወገን ድንበሬ ተገፋ እያሉ ለሱዳን ከሰጡት መሬት በለምነትም ሆነ በስፋቱ እምኑም የማይደርስ ቁራሽ መሬት ከሻቢያ አስጥላልሁ ብሎ ያገር አድን ጥሪ እያሉ ሆያ ሆዬ መጨፈር ሚስጥሩ ሊገባኝ አልቻለም ።
ለጎረቤት አገሮችም ሆነ ባሕርና ውቅያኖስ አቋርጠው ለመጡ የውጭ መንግሥታት አገር እየተሸነሸነ በሚሰጥበትና በሚቸበቸብበት በወያኔ አገዛዝ ዛሬ በድንበሬ ተገፋ ሳቢያ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ለመግጠም ለምን አስፈለገ? ኢትዮጵያዊው በርግጥ ጦርነት ማድረግ ካስፈለገው ጦርነቱን ማድረግ ያለበት ከወያኔ ከራሱ ጋርና ከድርቡሾች ጋር እንደሆነ ሕዝባችን ጠንቅቆ ያውቀዋል ። ባገር ተወረረ ሳቢያ ፤ በውዴታ የመጣን ጦርነት አንተርሶ ዛሬም ወያኔ እራሱን እንዳንታገለው ለኢትዮጲያ አንድነትና ዳር ድንበር አሳቢና ተቆርቋሪ በመምሰል ጦርነቱን ደጋፊና ፤ ጦርነቱን ተቃዋሚ በሚል ውዥንብር በሕብረተሰቡ ውስጥ በመንዛት ወደሱ የተነጣጠረውን ትግላችንን ለማዳከሚያና ትግሉን ለመከፋፈያ ሊጠቀምበት እንደሚፈልግ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልብ ሊሉት ይገባል ።
ይህንን የማዘናጊያ ጦርነት አላማውን ተገንዝበን ወያኔ ከሕዝብ ሊያገኝ የፈለገውን ድጋፍ እንዳያገኝ ጠንክሮ በመስራት በጸረ ወያኔነት የተሰለፈ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ግዴታ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል ። ነገሮች በየ ቀኑ እየተለዋወጡና መልካቸውን እየቀየሩ በመምጣታቸው እኛም በየጊዜው ወያኔ አጀንዳ እያቀረበልን ትኩረታችንን በመሳት የወያኔ ሰለባ ከመሆን እራሳችንን መጠበቅ ይኖርብናል ።
ይህ ጸረ ሕዝብና ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ አገዛዝ ስር እየሰደደ ፤ ኢትዮጵያዊነት ደብዛው እየጠፋ መጥቷልና የምንሰራውንና የምንቃወመውን በሰከነ አይምሮ መርምረን መንገዳችንን ማስተካከል ተገቢ ነው ። አገሬ ብለን የምንጠራት ፤ ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን የምናስተላልፋት ፤ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የመኖር አለመኖር ህልውናዋ ከምን ጊዜም በላይ አሳሳቢ እየሆነ ስለመጣ ፤ ነገ ሳይሆን ዛሬ ፤ ሳይመሽብን ስለ ሐገራችን መምከር ፤ መወያየት ጊዜ ልንሰጠው የማይገባ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን አምነንበት ከምን ጊዜውም በላይ እጅ ለእጅ ተያይዘን ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል እላለሁ ።
ድል ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ! http://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/02/09/62345/
No comments:
Post a Comment