Yakob's Point of Views and News, Ethiopian politics and News, Cultures, Musics etc

Thursday, May 9, 2013

ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድ! የዋና ኦዲተር ሪፖርት ይደመጥ! [አዲስ ዘመን]


Posted by Daniel Berhane on Wednesday, May 8, 2013 @ 12:13 am · 1 Comment 

(አዲስ ዘመን)
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የኢፌዴሪ ምክር ቤት ያፀደቀውን በጀት፣ የፋይናንስ አስተዳደር ሕግ እንዲሁም ደንብና መመሪያ በሚፈቅደው መሠረት በትክክል ሥራ ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል።
በምክር ቤቱ የተፈቀደላቸውን በጀት ሕጋዊና ተገቢ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋልም ግዴታቸው ነው።
ለሙስናና ብልሹ አሠራሮች በር የሚከፍቱ ሁኔታዎችን ማስወገድና ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራርም ማስፈን እንዳለባቸውም ይጠበቃል።በተግባር እየሆነ ያለው ግን በተፃራሪው ስለመሆኑ ሰሞኑን የዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2004 በጀት ዓመት ሂሳብ ላይ ያከናወነውን ምርመራ ተከትሎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ሪፖርት ያመለክታል።
እንደሪፖርቱ በርካታ የሂሳብ አያያዝ ግድፈቶችና የውስጥ ቁጥጥር ድክመቶች፣ እንዲሁም አፈፃፀማቸው ከደንብና መመሪያ ውጪ የሆኑ ሁኔታዎች መገኘታቸው ተደርሶበታል። ከኦዲት ግኝቶቹ መካከል
በፌዴራል መስሪያ ቤቶች:-
- ወደ 1ነጥብ4 ቢሊዮን ብር አልተወራረደም፤
- 313 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ዕዳ ሳይመልሱ የተሸጡ ድርጅቶች አሉ፤
- 897 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ህጋዊ ባልሆነ ክፍያ ወጪ ተደርጓል፤
- 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ከግብር ከፋዮች በስህተት የተሰበሰበ ገንዘብ፤
- በ30 መስሪያ ቤቶች 353 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ደንብና መመሪያን ያልተከተለ ግዥ ተፈጽሟል፤
- በ9 መስሪያ ቤቶች 3 ነጥብ5 ቢሊዮን ብር ባልተሟላ ሰነድ ወጪ ሆኗል፤
- በ27 መስሪያ ቤቶች ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ ብር 212 ነጥብ5 ሚሊዮን ተጠቅመዋል፤ የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው።
ከሪፖርቱ ለመረዳት እንደሚቻለው መስሪያ ቤቶቹና እነርሱን የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች የመንግሥትን አሠራርና መመሪያ ወደ ጎን በመተው መስሪያ ቤቶቹን መርተዋል ወይም አስተዳድረዋል ማለት ነው። አሠራሩ ተገቢና ሕጋዊ ባለመሆኑ የእርምት እርምጃ መውሰድ የግድ አስፈላጊ ይሆናል።
እንደሚታወቀው የዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት በፌዴራል መንግሥት በልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶች የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት ወቅት የታዩ ዋና ዋና ግኝቶች ለምክር ቤቱ በየዓመቱ ያቀርባል። መስሪያ ቤቶቹም አሠራራቸው ሕጋዊና መመሪያውን የተከተለ ይሆን ዘንድ ያሳስባል። ምክር ቤቱም አስተያየቱን በመስጠት እንዲስተካከሉ ይጠይቃል።
በየዓመቱ ግን ተመሳሳይ ነገር እያደመጥን ነው። በቢሊዮን የሚቆጠሩ ብሮች የሕጋዊ አሠራር ያለህ እያሉ ይጮኻሉ። ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትም በየዓመቱ ሪፖርት ያቀርባል። የሚሰማ ጆሮ ግን አልተገኘም ማለት ይቻላል። ስለዚህ የሚሰማ ጆሮና የሚቆነጥጥ አካል ሊኖር ይገባል ማለት ነው።
ስለሆነም በሪፖርቱ መሠረት የእርምት እርምጃ ባልወሰዱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ተገቢውን አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን በሚቀጥለውም በጀት ዓመት ተመሳሳይ ሪፖርት ለመስማት ፈቅደን ተቀምጠናል ማለት ነው።
የአስፈፃሚውን አካል የሚቆጣጠረው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰጠው ውክልና መሠረት ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል።ሪፖርት አዳምጦ መስተካከል አለበት ብቻ ብሎ ማለፍ የለበትም።
ምክር ቤቱ በእዚህ ጉዳይ የወሰደውን እርምጃም ለሕዝቡ ማሳወቅ ይጠበቅበታል። ሕዝቡ በ2004ዓ.ም የዋናው ኦዲተር ሪፖርት መነሻነት ችግር በተስተዋለባቸው መሥሪያ ቤቶችና የሥራ ኃላፊዎች ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደተወሰደ ማወቅ ይፈልጋል። ተገቢም መብቱም ነው።
አስፈፃሚው አካልም በምክር ቤቱና በሕዝብ የተሰጡትን ኃላፊነቶች በአግባቡ ሊወጣ፣አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶቹም የተሰጣቸውን ኃላፊነትና በጀት በአግባቡና ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ሊሠሩ ግዴታቸው በመሆኑ ሕግ አውጪው አካል ጠንከር ያለ ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅበታል።
የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ያሳዩ፣ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ ያለ አግባብ የተፈፀሙ ክፍያዎች፣ለንብረት ገቢ ደረሰኝ አለመቁረጥ፣የወጪ ማስረጃ ያልቀረበበት ሂሳብ፣የግዥ አዋጅ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ የተፈፀሙ ግዥዎች፣ የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለባቸው ሂሳቦች፣ በብልጫ የተከፈለ ወጪ፣ በገቢ ሂሳብ ሪፖርት ውስጥ ያልተካተተ ገቢና ሌሎች ግድፈቶች ለሙስናና ብልሹ አሠራር በር የሚከፍቱና ሙስና ያጠላባቸው በመሆኑ አስፈላጊውን አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ከአስፈፃሚውም ሆነ ከምክር ቤቱ ይጠበቃል።
የዋና ኦዲተር ሪፖርትን በአግባቡ አዳምጦና አጢኖ የቢሊዮን ብሮች በሙስና የመጥፋትን ጩኸት በማድመጥም ፈጣን የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው።
በተለይ በተደጋጋሚ ሕግ ደንብና መመሪያ ያልተከተለ አሠራር ተግባራዊ የሚያደርጉ መሥሪያ ቤቶችና ኃላፊዎች ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል።
ሕዝቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ከአስፈፃሚው አካል በእዚህ ዙሪያ የተወሰዱ እርምጃዎች የማወቅ መብቱ ሊከበርለት ይገባል።
ከድህነት ለመውጣት የሚያደርገውን ትግል በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የአገር ሀብት በግለሰብ የሥራ ኃላፊዎች ቸልተኝነት ድክመትና ብልሹ አሠራር ምክንያት ለአደጋ መጋለጥ የለበትም።ስለሆነም የዋናው ኦዲተር ሪፖርት ይደመጥ፤በጥፋተኞች ላይም ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድ!

No comments:

Post a Comment