Yakob's Point of Views and News, Ethiopian politics and News, Cultures, Musics etc

Wednesday, March 20, 2013

አገሪቱ የተጠመደችባቸው ውስብስብ ችግሮች!

ስለኢትዮጵያ በአጠቃላይ ምን ያልተባለ፤ያልተጻፈ አለ? ምን አዲስ ነገር ሊጻፍ ይችላል? ከሚሆሉ ነገሮች በስተቀር፤ ስለ አገራችን ያልተጻፈ ጉዳይ የለም። ሁሉም በየፊናው የተቻለውን ብሏል፤ጽፏል። አዲሱ፤ይህ መዘዘኛ ስርአት በየቀኑ እየፈለፈለ የሚያወጣቸው ፤የተደመሩና የተከማቹ፤ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚፈነዱ የፖለቲካ ፈንጂውች እንጂ ሁሉም ተብሏል። አንድ ጉዳይ ግን እወነት ነው፤የሚጻፉ የተባሉ ሁሉ የተመሳሰሉ ቢሆኑም የቆሙበትንና የመፍትሔ ፍለጋ ላይ በአጽንኦም ተግባራዊነቱ ላይ ብዙ ፈታኝ ምእራፎች ተደቅነው ይታያሉ። 
 
የኢትዮጵያ ችግር አንድ ሁለት ተብሎ የሚዘለቅ አይደለም። ለዘመናት በተለያዩ ስርአቶች የተፍጠሩ፤የተከማቹና ውስብስብ ለመፍትሄል አስቸጋሪ የሆኑ ናቸው። 

ከዚህ በታች በጥቅሉ የተቀመጡ አሳቦች አዲስ ሳይሆኑ የነበሩ ናዘው። ለምን መጥቀስ አስፈለገ ቢባል፤ የጉዳዮቹን ፈታኝነትና የሚያመለክቱትን አደጋ አጢኖ ግንዛባ ለመውሰድ፤ ብሎም መፍትሄ ለማፈላለግ ቢረዳ ተብሎ ነው። የተዘረዘሩት ባመዛኙ ስርአቱ የፈጠራቸው፤ያገነናቸው ቢሆኑም፤ በቅድሚያ ስርአቱ፤ ያለፉት ስርአቶች፤አጎራባች አገሮች፤አለማቀፍ ሁኔታዎችና፤ ሳይጠቀስም መታለፍ የማይችሉት በጅምላ በተቃዋሚነት የተሰለፉ ባገርም፤በውጭም፤በሰላምም፤ባመጽም የሚታገሉ የተሰባሰበውና የተበታተነው ሐይሎች ጭምር ናቸው። ብዙ የማያናቁሩም ባይሆኑ፤ በየፈርጃቸው መጠቃልለ ያለባቸውም ቢመስልም፤ ለመቃኘት ያክል አሉ የሚባሉ ፈታኝ ምስቅልቅሎቻችን ምን ይመስላሉ።

1. ዘረኝነትና መዘዙ፤
በአይነታቸው አስከፊ ከተባሉት በደቡብ አፍሪካና በሌሎች አካባቢ ከታዩት ባልተናነሰ፤እንዲያውም አገር በቀል በመሆኑ የከፋ ያንድ አናሳ ዘር የበላይነትና ጉዳዮችን በራሱ የስልጣን ጥምና ጥቅም ዙሪያ እያሽከረከረ በአሁኑ ወቅት ፈታኝ ችግሮችን ደቅኗል። ያለው እንዳለ ሆኖ የሚያመጣውና፤ እያመጣ ያለው መዘዝ በቀላሉ ለመወጣት የሚቻል አይደለም። ስር ሰዶ፤ፍሬ አፍረቶ ውጤቱ በሕዝቦች መካከል አለመተማማን፤መቃቃር፤ መጋጨት፤መፈናቀልን ፍጠሮ ጉዳዩ አሳሳቢ ሂኔታ ላይ ደርሳል። ዘለቄታውስ ምን ይሆን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ቢሆንም፤ ማንም መገመት እንደሚችለው እትዮጵያ እንደአገር ልትቀጥል የምትችልበትን መሰርት ያናጋና አደጋ የደቀነ አብይ ችግር ሆኗል። በነጻንተ ከሚገኝ አንድንት ይልቅ የጠመንጃ ሐይል ፊት ካሰከተለው የተለየ ውጤት የለውም። ሌሎቹ ያገር ችግሮች ይህን ለበለጠ ጥፋት ይመግቡታል እንጂ አይቀርፉትም።

2. የመልካም አስተዳዳር እጦት፤
ያለው ስርአት ሁሉንም የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤የማህበረሰብና በሐይማኖት ሳይቀር አጠቃላል የአስተዳደር እርከኑንና አስከ ቤተሰብ ድረስ ዘልቆ በማፈን ህዝም እንዳይናገር፤እንዳይጽፍ፤ እዳይሰበሰብ፤ በነጻነት እናዳያመልክ ጠፍሮ ቀፍድዶ አደንዝዞ በገዛ አገሩ ባይተዋር የበዬ ተመልካች አድርጎት ለመዝለቁ የሚያጠያይቅ አይደለም። አገሪቱ በተከታታይ የሶስት ስርአቶች የንጉሥ፤ያምባገንንና የዘረኛ ስርአት ሰለባ ሆና ሕዝብ መከራውን ሲጋት፤ አገር ስትፍርስአ፤ አንድነት ሲሸረሸር፤ ጥፋት ሲመርት ለማየት በቅተናል።

3. ድህነት፤
ዛሬ አትዮጵያ ብዙዎች የሚራቡባት፤ ሉሮ ያሸቆለቆበባት፤ ድህነት አገርንና ህዝብን የአለም ጭራ ያደረገበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። በአንዳሩም ጥቂት ባስተዳደር እርከኑ ላይ የተንጠላጠሉ አናሳውና አጋፋሪዎቹ ሀብት አካብተው ትላንት የመጡበትን ብቻ ሳይሆን ነገ የሚሄዱበትን እጣ ፍንታቸውን ለማየት የተሳናቸው አዲስ የበላታና ቡድን መፈጠሩ ነው። አብረን ሠርተን አብረን እንጠቀም ሳይሆን ሊሠራ የሚችለውን እጅ የሚያስር፤ አቅም ያለውን የሚያመክን የስግብግቡችን ጥርቅምን ፈጥራል። ድህነት የችግሮች ሁሉ መሰረት ነው። የህዝብ ድህነት ሲንር ዝም ከማለት ባሸገር አመጽን፤ ምንም ማንም ሌያግደው የማይችለውን ማእበል ይወልዳል። በመሥራት ማደግ መበልጽግ ሲቻል በዝርፊያ ድሀ፤የድሀ ድሀ ያደረጉት ተጠያቂዎች ናቸው። ያገሪቱን ሀብት የተፈጥሮ ለም መሬተና ማእድናቱን ባልባሌ አስተዛዛቢ፤ሚዛን በጎደለው አስተሳሰብ ለባእድ አሳልፎ መስጠት ወንጀል፤ ያገር ክህደት የከፋ ወንጀል ነው።

4. ዝረፊያ - ኪራይ ሰብሳቢ ስርአት(ኮረፐሺን)፤
ምንጩ ከደፈረስ የጠራ ውሀ የለም። በአገሪቱ ዝርፊያ አይን ያወጣ ሙሰኝነት፤ ጥቅምን ማግበስብስ ፤ ያገሪቱ ሀብት በተለያየ መልኩ በሚታይና በማይታይ ስልት ወደ ውጭ እየጎረፈ ለመሆኑ፤ ከድሀ አፍ እየተነጠቀ ለመንጎዱ ብዙ ዋቢዎች በይፋ እየቀረቡ ይገኛሉ። ሕዝብ ይህን አያውቅም አይሰማም አረዳም፤ የመስሚያ የመረጃ አውታሮች ሁሉ ታፍነው ህዝብ የራሱ ጉዳይ ባይተዋር ሆኗል። በቀላሉ አደንዝዘውታል። ኪራይ ሰብሳቢነት ሌላ ትርጉም አያሻውም፤ ስርአቱን በማፈኛነት በመጠቀም መበልጸግ ብቻ ነው። በቀላሉ አይን ያወጣ እፍረት የጣ ዝርፊያ። የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀሰው ባንጋፋ በስርአቱ በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችና በጣት በሚቆጠሩ ግለሰቦች መሆኑ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ተግባር ነው። በሰርአቱ ስር የተሰገሰጉ፤ጊዜ የሚገልጣቸው የማይመስላቸው ከተጠያቂነት ማምልጥ አይችሉም። በንጽህና መበልጸግ አለ፤ በዝርፊያ ግን በማንናቸውም መልኩ ያስጠይቃል። ከሁሉም የበለጠ ሓጢአት ነው። እግዚአብሔር ድሃ ሲያለቅስ አይወድም። ስላላመኑም ከቅጣት ማምለጥ የለም።

5. የሀይማኖት ነጻነት መጥፋት፤
አደጋውች በየፈርጁ ተኮልኩለዋል። የተደማመሩ ቀውሶች መዘዛቸው የከፋ ነው። ጳጳስ ፈንቅሉ የእምነት አውታሩን ከመቆጣጠር፤ የእምነትን ህገደንብ ለውጦ ሌላ እምንት ፍጥሮ፤ባማኙ ላይ መጫን፤ ለስልጣን፤ ለጥቅም ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ነው። ገዳመት ተገለበጡ፤ ንጹህ አባቶቻችን ተዋከቡ፤አለቀሱ፤ተሰደዱ፤ለመከራ ተዳረጉ። በእምነት ጣልቃ ገብነት መዘዙ፤ ይህ ተፈጥሮ ያመጣችው ነው ተባለም አልተባለ፤ከላይ የመጣ መአት ሊፈስ ይችልል። ለተረዳውም የሆነውን አይተናል። በሌላ መልኩ፤ ተስማምቶ ተከባብሮ ባንድነት የኖረውን ሕዝም ፈተና ውስጥ ከቶታል። ከግፊትም ብዛት ሰላማዊውን ሕዝም ወደ አላስፈላጊ ጎዳና ይመራዋል፤ አመጽም ይባል ሽብር ይቀፈቅፋል። በዚህም ሆነ በዚያ እሳት ይጭራል፤ እልቂት ይጋብዛል። ጠመንጃም ሊየግደው የማይችል የሕዝብ ማእበልን ይወልዳል።

6. አካባቢ አጎራባችና ተዛማችች፤
ለችግሮቻችን መፍትሄ ሳይሆን እሳቱን ጭድ የሚመግቡ ሀይሎች ብዙ ናቸው። ኤርትራረ የሰበሰበቻቸው በአብዛኛው አገርን አንድነት የሚያናጉ ሀይሎች ከዚሁ ይመደባሉ። የተዳፈነ እሳት ይምስል እንጂ ቀውስ ሲመጣ እነዚህ ሀይሎች በአራቱም ማእዘናት እሳት የሚያነዱ የተደቀኑ አደጋዎች ናቸው። ኤርትረም ለኤትዮጵያ ሳይሆን ለረሷ ደህነት፤ በከፊልም የቂም መወጫ መንገዷ እንደሆነም መዘንጋት የለበትም። ከውጭ የሚርገበገቡ ሽብርተኝነትን የሚቀሰቅሱና የሚመግቡ ሂደቶችም ሌላዎቹ ችግሮች ናቸው። የግድቡ ውጥንቅጥም አንድ እራሱን የቻለ ፈተና ነው:፡ አባይ መገደቡን፤አገር መልማቷን፤ ሕዝብ መበልጸጉን የሚጠላ ኢትዮጵያዊ የለም። ጥያቄው ልማት ከማን እጅ እንዲትና ለማ የሚሉት ናቸው። ያገሪቱን የአመት በጀት በሚያክል ንዋይ፤ ግዝፈቱ ለፍጻሜው አደጋ የሚጋብዝ ትልም፤ ከአካባቢውና አጎራባች አገሮች ጋር ለዘለቄታው የሚያፋርስ፤ ጦርነትን የሚጋብዝ የልማት ትልም ለሁሉም ፈታኝ ነው። ይህ አገርን የመውደድና የመጥላት ጉዳይ አይደለም ያገር የዘላቂ ደህንነት እነጂ።

7. የምእራቡ ትጽእኖ፤
ምስራቡን በእጅጉ ታዝበነዋል። ለነገሩ ነው። ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ የሆነ ነገር። የሕዝቡን ጥቅም መብትና ነጻነት፤ ያገሪቱን ደህንነት ወደጎን በመተው ከሟቹ ጋርና አሁንም አንድ በመሆን፤ከመፍትሄ ይልቅ ለሕዝብና ለአገር ስቃይ መራዘም አስተዋጽኦ መሆኑ አሌ አይባልም። ይባስ ብሎ በበለጠ ሊያስደንግጣቸው በሚችል ሁኔታ አሁን የሚታየው የሐይማኖት ማእበል፤ የበለጠ የሚያሰጋቸው፤ ስርአቱን ይበል የሚሉበትን ሁኔታነ የሚጋብዝ ለው። ምእራቡ ከፊቱ የበለጠ ምእራብ ሆነ ማለት ይቀላል። ዲሞክራሲና ለሕዝብ መብትም መቆርቆር ካባ ልምስ እንጂ ጥቅም ቅዲሚያን ይዛ ነጉዳለች። ዘመኑም የከፋ ነው!!!!

8. የተቃዋሚው አካሄድ፤
እንግዲህ አልቀሬ! ከየትኛው ቡድን! እንበላ። ከችግሩ ወይስ ከመፍተትሔው? ስርአቱ-በአመዛኙ፤ሊሎችም ተጠያቂ ቢሆንም፤ ተቃዋሚው መፍትሔ ለመሆን በሚያደርገው ጥረት ለችግሮች እይተኛ አስተዋጽኦ መሆኑ ሳይወጠቀስ ሊታለፍ አይገባም። የተቃዋሚው ችግር አንድና አንድ ብቻ ነው። መሰባሰብ በአላማና በመርህ ባንድ ላይ አለመሆን!!!! ሌላ ላይደለም፤ጂኦግራፊም አቅምም ሌላም ሌላም ቢጠቀስ፤ ሕዝብን የሚአክል ሃይል፤ አገርን የሚያክ ጉዳይ ይዞ መዘናጋት ድክመት ብቻ ሳይሆን አተጠያቂነት ውስጥ መመደቡ አይቀሬ ነው።
ታዲያ፤ኢትየጵያ ይህን ሁሉ፤ ከዚህም በዘተረፈ ያልተጠቀሱ የዘማናት ፈተናዎችን ቀፍቅፋ ታቅፋለች። ተሸፋፍኖ መተኛት ችግሮችን አያጠፋም፤ ያባብሳል እንጂ። እስካሁን በእያንዳንዱ አእምሮ ውስጥ መፍትሔ የሚል ደወል መቃጨሉ አይቀርም።
ምፍትሄው በቅድሚያ ካለው አስተዳደር፤ ከምእራቡና ከሌሎች አይገኝም። መፍትሔው ያለው ከሕዝቡና ፋና እያበሩ፤ ፈር እየቀደዱ አቅጣጫን በሚሰጡት፤በሚጠቁሙ ልጆቹ እጅ ነው። 


ገና በጥዋቱ፤ በደርግ ጊዜ ማለት ነው፤ ገበሬው ከገጠር ዱላውን የሽቅብ እየዶለ ሆ!ሆ!ሆ! እያለ አደባባዩን በሞላበት ወቅት፤ አንድ የውጪ ዜጋ "ይህ ሁሉ ዱላ ወደጠመንጃ ሳይለወጥ እግራችሁን አውጡ" ብሎ በአገር ጋዜጣ ጽፎ ነበር፤ ወገኖቹን ማለቱ ነው። ሐቁ ይኸው ነው፤ የያዘን አባዜ ቀላል አይደለምና ምሳሌው ሁሉን ይናገራል። አገሪቱ ድህንተ የለባትም፤ሁኔታዎች አደኸይዋት እንጂ። የሰው-በያይነቱ፤የተፈጥሮ ሓብት ባለጸጋ ናት። ይህ ሆኖ ሳለ፤ ለዚህ ሁሉ ቀዳሚ መፍትሔ የሚሆነው መልከም አስተዳደር መሆኑ አይዘነጋም። መሰባሰብ ማሰባሰቡም ለዚሁ ነው። ስልታጣንም፤ የመልካም አስተዳደር ባለበት ማለት ነው፤ ከህዝም እንጂ፤ ከእንግዲህ አገሪቱም፤ሕዝብም፤ ጊዜውም ሌላ የጥፋት ስርአት አይፈልጉም። ሁኔታዎችን እንደነበሩ እንዳሉ በመርገጥ መቀጠል የጤንንት ምልክት አይደልመ። ጥቅምም፤ጊዜም፤ሰውም ያልፋሉ፤ አገርና ትውልድ ይቀጥላሉ። ይህ ሁሉ ሲያልፍ ለአድራጊዎች የሚሰጣቸው ስም ምን ይሆን? ጊዜ ምስክር ትሁን-ካለች ማለት ነው።

ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር፤በሕዝቧና በሓቀኛ ልጆችዋ ትድናለች! 

 ቸር ይግጠመን!!
ፍ.አ.
03 13 13

No comments:

Post a Comment