Yakob's Point of Views and News, Ethiopian politics and News, Cultures, Musics etc

Tuesday, December 11, 2012

የጦር ሃይሎች ጠ/አዛዥ ማነው?

(ከኢየሩሳሌም አርአያ)
በከፍተኛው ፍ/ቤት ዳኛ ሆነው ለረጅም ዓመት አገልግለዋል፤ ከዚያ ከለቀቁ በሁዋላ
በጥብቅና ሙያ እየሰሩ ይገኛሉ። ታዋቂው የህግ ባለሙያ አነጋጋሪ በሆኑ የኢህአዴግ
የፈጠራ ክሶች ዙሪያ ለተከሳሾች ጥብቅና በመቆምና በድፍረት በመሙዋገት ይታወቃሉ።
በ1997 ከአንድ የፈጠራ ክስ ጋር በተያያዘ ለተከሳሾች ጥብቅና ቆመው ነበር፤ በፌደራል
ጠ/ፍ/ቤት በተሰየሙ ዳኛ ተብዬዋች ተግባር ክፉኛ የተበሳጩት እኚህ የህግ ባለሙያ
በወቅቱ እንዲህ አሉኝ፥
« በንጉሱ ዘመን ነው፤ በአ.አ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ልንመረቅ ሽር ጉድ እንላለን። የምንወደው
የህግ መምህራችን የኛን ሁኔታ ታዝቦ ኖሮ...አንድ ጥያቄ አቀረበልን፤ “ አሁን ሳያችሁ
በደስታ እንደተዋጣችሁ ነው፤ በመመረቃችሁ ደስተኛ ናችሁ ማለት ነው?... “ ሁላችንም
በጥያቄው ተገርመን ..< እንዴት መምህር?..በጣም ደስተኞች ነን ፤ > አልነው። ደግሞ
ጠየቀን ፥ “ ሁላችሁም ደስተኞች ናችሁ?”..ሲለን..< አዎን ደስተኞች ነን > አልነው
በአንድ ድምፅ። በጣም አዝኖ እንዲህ አለን ፥ < ሕግ በሌለበት አገር ህግ ተምራችሁ
..ሕግ የምታስፈፅሙ ይመስል፥ እንዲህ መደሰታችሁና መመፃደቃችሁ ታሳዝናላችሁ.!>...
ዛሬ የበለጠ የመምህራችን ንግግር ታወሰኝ፤ እውነትም ሕግ በሌለበት አገር...» ሲሉ
ታዋቂው የህግ ባለሙያ ያወጉኝን ለመጣጥፌ መንደርደሪያ ማስቀደሜ ያለምክንያት
አይደለም።
ጠ/ሚ/ር ተብለው የተቀመጡት ሃ/ማሪያም ደሳለኝ የጦር ሃይሎች ጠ/አዛዥነቱ ስልጣን
አልተቀበሉም። ቀደም ሲል ይህ ስልጣን በአቶ መለስ እጅ ነበር። እንዲያውም የከፍተኛ
ጄኔራሎች ሹመት በተመለከተ ቀደም ሲል የነበረውን ሕግ በመሻር ስልጣኑን ጠቅልለው
የያዙት አቶ መለስ ነበሩ። ይህ የተደረገው ከ1993ዓ.ም ወዲህ ነበር፤ ከዚያ በፊት ግን
የጦር አዛዦችን ሹመት የሚያቀርበው ጠ/ሚኒስትሩ ሲሆን የሚያፀድቀውና የሚሽረው
ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ነበር። ፕ/ት ነጋሶ ከስልጣን ለመልቀቅ የወሰኑበት አንዱ ምክንያት
ይህው ነበር። ከሳቸው እውቅና ውጭ ጠ/ሚ/ሩ ጄኔራሎችን በማባረራቸው እንደነበር
ይታወሳል። ከዛ በሁዋላ አቶ መለስ ስልጣኑ ሙሉ በሙሉ የጠ/ሚ/ሩ እንዲሆን
የሚያስችል ህግ አውጥተው አረፉት። የሚሽሩትም የሚሾሙትም እርሳቸው ሆኑ። ባለፈው
ጊዜ ጠ/ሚ/ር ሳይኖር 34 ጄኔራሎች መሾማቸው ተነገረ፤ አስገራሚና አነጋጋሪነቱ እንዳለ
ሆኖ ለዚህ የተሰጠው መልስ ይበልጥ አስቂኝ ነበር። « ቀደም ሲል በጠ/ሚ/ሩ የተዘጋጀ
ነው» ብለው በረከት ተናገሩ። ከተሾሙት መካከል መለስ ለሹመት ለአፍታ ሊያስቡዋቸው
የማይችሉ መኮንኖች መኖራቸው የበረከት መልስ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ታዛቢዋች
በወቅቱ አስተያየት የሰጡበት ነው።
አሁን ደግሞ « የጦር ሃይሎች አዛዡ ማነው?» ተብሎ ቢጠየቅ መልስ የለም። ሕጉን
እንቀበል ቢባል እንኩዋን ስልጣኑ በጠ/ሚ/ር ሃ/ማሪያም እጅ አይደለም። አሁን አገሪቱዋን
የሚመራው የጦር ሃይሉ ጠ/አዛዥ ማነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ተጨባጭ መልስ መስጠት
አይቻልም። ስልጣኑ በዘፈቀደ የተለያዩ የሕወሓት ጄኔራሎች እና ባለስልጣናት እንዲሁም
ከመጋረጃው ጀርባ ባደፈጡ የድርጅቱ ባለስልጣናት እጅ እየተሽከረከረ እንዳለ መረጃዋች
ይጠቁማሉ። ለመጥቀስ ካስፈለገ ባለፈው ወር በሳሞራ ቀጭን የስልክ ትዕዛዝ የተነሱት
ጄኔራል...በአስገራሚ ሁኔታ እንዲመለሱ የተደረገው ከጀርባ ሆነው አንድ ቡድን
በሚያሽከረክሩት ስብሃት ነጋ እንዲሁም ሌሎች ተከታዮቻቸው ርብርብ ነው። በተነሱት
ጄ/ል የተተኩት እንዲነሱ የተደረገውም በዚሁ ቡድን ጣልቃ ገብና ሕገ-ወጥ ውሳኔ ነው።
ሕግ፡አዋጅ...የሚባል ጨርሶ አይሰራም!! ከዚህ በተጨማሪ 3 ጄኔራሎችን ጨምሮ በርካታ
የበታች መኮንኖች ታግደው..ውሳኔ እየጠበቁ ነው፤ ከታገዱት ከኦህዴድ ወገን ይበዛሉ።
ይህ ሁሉ እየተደረገ ያለው በጄ/ል ሳሞራና ከሳቸው ጋር በተሰለፉ የቡድን አባላት ሲሆን
በተቃራኒ ያለው ቡድንም የራሱን የማባረርና የማስመለስ ድራማውን ገፍቶበታል። ይህ
ሁሉ የሚከወነው የሃ/ማሪያምን በአዋጅ የተቀመጠ ስልጣን በአደባባይ በጡንቻ በመውሰድ
ወይም በመግፈፍ ነው። ጠ/ሚ/ሩ < ለምን?..እንዴት.. ከኔ እውቅና ውጭ..? >
ብለው ለመጠየቅ ይቅርና የሚያስቡት አይመስልም። አይተው እንዳላዩ መሆንን
መርጠዋል። ከዚህ ይልቅ የመለስን «ካባ» አጥልቀው « ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር አስመራ
ሄጄም ቢሆን እነጋገራለው፤ እደራደራለው» ማለቱን ተያይዘውታል። ይህም ቢሆን
የርሳቸው ውሳኔ ሳይሆን ከጀርባ ያለው ሃይል የቆየ ፍላጐትና እመነት ነው። ብዙ ወገኖችን
ያስገረመው ጉዳይ ባለስልጣናቱ ለሻዕቢያ ባለስልጣናት የሚያቀርቡት ልምምጥ የሚታይበት
የድርድር ጥያቄና ተማፅኖ፥ በአገር ውስጥና በውጭ ላሉ ተቃዋሚዎች ለአንድ አፍታ
ሊቀርብ ቀርቶ ያለመታሰቡ ነው። ከዚህ ይልቅ « ድርድር አይታሰብም» ከሚለው
አንስቶ..« የሻዕቢያ ተላላኪዎች፡ ፀረ-ሰላም ሃይሎች..አሸባሪዎች..» የሚል ያልተጨበጠ
ታርጋ እየለጠፉ መወንጀል፡መዝለፍና እስር ቤት መወርወርን ስራዬ ብለው የገፉበት
ተጨባጭ እውነታ ነው የሚታየው። የገዢዎቹ ሃሳብና ድርጊት እንደሚጋጭ የሚሳየው «
ሻዕብያን ፀረ ሰላም ሃይሎችን በዋና አዛዥነት የሚመራና የሚያሰማራ..» እያሉ እየፈረጁ፥
በአንፃሩ ለሻዕብያ የድርድር ጥያቄ አቅራቢዎች ደግሞ እራሳቸው መሆናቸው ብዙዎችን
ያስገረመ ሆኖዋል። ሲጠቃለል፥ ኢህአዴግ ራሱ ላወጣውና ለሚመፃደቅበት « ሕገ
መንግስትና አዋጅ» ተገዢ መሆን አልቻለም። ይባስ ብሎ ሁሉም አዛዥና ፈላጭ ቆራጭ
ሆኖዋል። የአቶ ሃ/ማሪያም ስልጣንና ሚና ውሉ አልለየም። የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ዋና
አዛዥ ከአገሪቱ ቁልፍ ስልጣኖች ዋናው ነው። ማን ጋር ነው? የሚለውን ጥያቄ ከላይ
ለማመላከት ተሞክሮዋል። ጥያቄው ግን አሁንም መነሳቱ ይቀጥላል። ጠ/ሚ/ሩ አውቀው
ተኝተዋል። ይህ ስልጣን በየፊናው የሚያዝበት ስለበዛ..ወዴት ሊወስድ
ይችላል?..የሚለው ለመገመት አያዳግትም። እየታየ ያለውም ይህንኑ ግምት የሚያጠናክር
ነው!!

No comments:

Post a Comment