Yakob's Point of Views and News, Ethiopian politics and News, Cultures, Musics etc

Wednesday, January 9, 2013

ታላቅዋን ትግራይ እውን ለማድረግ የወያኔ መሰሪ እርምጃዎች !!

አደፍርስ ተሰማ
መቸውንም ቢሆን ጠባብ ብሄርተኞች ሁሉን አቅፍ የሆነ አመለካከት እንደሌላቸው እማኝ መቁጠር አያስፈልግም። ወያኔና ሻቢያ የትግል ጽዋን የተጎነጩት ብሄርተኝነትን ተገን አርገው ነው። ለሰላሳ ዓመታት ወንድምና እህቱን በነጻነት ስም የጨፈጨፈው ሻብያ ዛሬ አስመራ ላይ ተጎልቶ የኤርትራን ህዝብ አፍኖ መተናፈሻ አሳጥቶታል። ወያኔ ከቁራሽ በተረፈቸው ኢትዮጵያ ምድሪቱን በክልልና በጎሳ በመከፋፈል ዝርፊያውን አጧጡፎታል።
ትግራይን ሃገር ለማረግ ከበረሃ ጀምሮ ያለመው ወያኔ አሁን እንሆ በሚኒሊክ ቤተመንግስት ራሱን ካስጠጋ ወዲህ ይህን ህልም እውን ለማድረግ መሰሪ እርምጃዎችን በህቡዕና በገሃድ ማራመድ ጀምሮአል። ከአጎራባች ክፍላተ ሃገራት ለም መሬቶችን እየቆረሰ ወደ ትግራይ የመሬት ይዞታ መጨመር፤ የውጭና የሃገር ውስጥ የልማት እቅዶችን የላቀ ድርሻ ለትግራይ ማደል፤ ልዪ ልዪ የትምህርትና የጤና ተቋማትን በትግራይ ማቋቋም፤ የባንክና የተለያዪ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶችን በተፋጠነ ሁኔታ በትግራይ ማመቻቸት በሃያ አመት የግዛት እድሜው ወያኔ የነደፈው የታላቅዋ ትግራይ ህልመ – ዓለም እቅድ ነው።
አሁን ደግሞ የሚናፈሰው የቀኑ ወሬ እንደሚጠቁመን OIA (Overseas Infrastructure Alliance of India) የተባለ የህንድ ኩባኒያ ከመቀሌ ወደ ጅቡቲ አድርሶ መላሽ የባቡር ሃዲድ ለመገንባት እንዳቀደ ይጠቁማል። ሥራውም ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሻ ተነግሮናል። የኢትዮጵያን ታህታይና ላዕላይ የኢኮኖሚ መዋቅር ጉሮሮ አንቆ የያዘው ወያኔ በመላ ሃገሪቱ ስም በልመናና እርዳታ የሚመጣን ንዋይ ለትግራይ ክልል ብቻ ማዋሉ የሚያስገርም አይሆንም። አቶ መለስ እኮ ተናግረው ጨርሰውታል። ከወርቃማው የትግራይ ህዝብ ተወልደዋል። ከእጣት እጣት ይበልጣል ይሉታል እንዲህ ነው። ይህ በበረሃና በከተማ በስሙ የተነገደበትና የሚነገድበት የትግራይ ህዝብ እዚህ ግባ የሚባል ጠቀሜታ ከወያኔ አልደረሰውም። ደልቶት የሚኖረው የወያኔን ጥሩንባ ነፊና አስነፊ ብቻ ነው። ሌላው ዛሬም ይታሰራል፤ ይገረፋል፤ ይታፈናል፤ይገደላል፤ ቤቱ ይፈርሳል። የትግራይ ህዝብና ትግራይ የወያኔ ኮሮጆ እንዲሞላ የሚጠቀምበት ሽፋን እንጂ ልጆቹን፤ሚስቱን፤ ባልዋን ለወያኔ ትግል የገበሩት ዛሬም ኡኡታቸው ሰሚ አግኝቶ ትርፍ አልተሰፈረላቸውም። ትላንት ያለቀሱ አይኖች ዛሬም እንባን ያፈሳሉ።
ታዲያ ሰፊው የትግራይ ህዝብ ድርሻው ሰቆቃ ብቻ ከሆነ ወያኔ ለምን ሁሉን ነገር ወደ ትግራይ ያመቻቻል? የወያኔ የረጅም ጊዜ አላማው ህዝብን ከህዝብ ጋር እያጋጨ የስልጣን እድሜውን ማራዘም ነው። ለዚህም ክፉ አላማው የተጠቀመበትና አሁንም የሚጠቀምበት ትግራይንና የትግራይን ህዝብ ነው። ለዚህ ህዝብ እዪን የባቡር መንገድ አስገባንላቹ፤ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋማትን ገንባን፤ በህዝባችን ላይ ተጭኖ የነበረውን የደርግ ቀንበር አስወገድን በማለት እየለፈፉ የእድሜ መለመኛ ኢንሹራንስ ነው እንጂ የትግራይ ህዝብ አፉን ታፍኖ እኛ እናውቅልሃለን ከተባለ ዘመን ቆጥረናል።
በዚህ ሁሉም ነገር ወደ ትግራይ ለትግራይ በሚለው የወያኔ ጠማማ ሃሳብ ዛሬ አትራፊ የሆኑ ሁሉ ቀኑ ሲመሽ መደበቂያ አይኖራቸውም። አዕላፍ ህዝብ እያለቀሰና እየተራበ ጥቂቶች በድሎትና በምቾት የሚኖሩባት አለም እድሜዋ አጭር ነው። ወያኔም ልብ ገዝቶ ዘርና ጎሳን ተገን ላለማድረግ ንስሃ ገብቶ ዝርፊያና ግድያን አቁሞ ሁለገብና ሁሉን አቀፍ፤ የመናገር የመጻፍ፤ የመሰብሰብ ነጻነት የሚኖራትን አንድ ኢትዪጵያን መገንባት እስካልቻለ ድረስ አወዳደቁ የሮም አወዳደቅ ነው የሚሆነው። አሁን የምንኖርባት ዓለማችን ለዘረኞች ሥፍራ የላትም።
የሚመጣውን ሰንብተን እንይ!
http://www.ethiopianreview.com/amharic/?p=10163
posted by Aseged Tamene

No comments:

Post a Comment